በቀጣይ ዘጠኝ ቀናት ደቡብ ምእራብ፣ ሰሜን ምዕራብና መካከለኛው የሀገሪቷ አካባቢዎች የተሻለ የዝናብ መጠንና ስርጭት ያገኛሉ

98
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 ከትናንት ጀምሮ በቀጣይ ዘጠኝ ቀናት በደቡብ ምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብና በመካከለኛው የሀገሪቷ አካባቢዎች የተሻለ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖር ብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጄንሲ አስታወቀ። በሌላ በኩል ደግሞ በሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ  ላይ አልፎ አልፎ ከሚኖር መጠነኛ ዝናብ በስተቀር ደረቅና ሞቃታማ የአየር ሁኔታ እንደሚያመዝን ኤጄንሲው በላከው መግለጫ  አመላክቷል። በኦሮሚያ ክልል  ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ አብዛኛዎቹ የሸዋ ዞኖች፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ በተጨማሪም የአርሲና የባሌ ዞኖችና አዲስ አበባ ከመደበኛው ተቀራራቢና የሚበልጥ ዝናብ እንደሚታይባቸው ኤጄንሲው አመልክቷል። በአማራ ክልል  ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች፣ የሰሜንና የደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ የባሕር ዳር ዙሪያ፣ ሰሜን ሸዋ፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች ፣ ሁሉም የትግራይ ዞኖች፣ ከአፋር ክልል ዞን 3 እና 5 ፣ የጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዞኖች ከመደበኛው የተቀራረበና  አልፎ አልፎም በጥቂት ቦታዎች ላይ ከመደበኛው በላይ ዝናብ ይጠበቅባቸዋል። በተመሳሳይ  በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል  የሀድያና የጉራጌ ፣ የወላይታ ፣ የከፋና የቤንቺ ማጂ፣ የሲዳማ  እንዲሁም ጥቂት የሰገን ሕዝቦች  ዞኖች ከመደበኛው የተቀራረበና  አልፎ አልፎ በጥቂት ቦታዎች ላይ ከመደበኛው በላይ ዝናብ ያገኛሉ። ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚቀጥሉት ዘጠኝ ቀናት የደመና ክምችቶች  እንደሚጠናከሩ ያስታወቀው ኤጄንሲው፤ በዚህ ሳቢያ በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው  ዝናም ሊከሰት  ይችላል ብሏል። በአንጻሩ ሌሎች የሀገሪቷ ዞኖች ደረቅ ሆነው ይሰነብታሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሕ የአየር ትንበያ በክረምት ተጠቃሚ አካባቢዎች ለሚከናወነው የግብርና ስራ መልካም አጋጣሚ እንዳለው የገለጸው ኤጄንሲው፤ በተወሰኑ አካባቢዎች የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ የአፈር መሸርሸርና የመሬት መንሸራተት ሊያስከትል እንደሚችል ታውቆ ተገቢው ቅድመ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብሏል። በመሆኑም የሚስተዋለው ዝናብ በበልግ ወቅት የደረሱ ሰብሎችን እንዳያባክን ተገቢው ጥንቃቄ ተወስዶ የሰብል መሰብሰብ ተግባራትን ማከናወን ይገባል ነው ያለው። የክረምቱ እርጥበታማ ሁኔታ በአብዛኛው የሀገሪቷ ተፋሰሶች  ላይ ሰፋ ያለ መልካም ጎን በማሳደር የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ ተፋሰሶችም የተሻለ እርጥበት አንዲያገኙ ያስችላል ብሏል ኤጄንሲው። በዚህም መሰረት የኦሞ ጊቤ፣ ባሮ አኮቦ፣ ተከዜ፣ የላይኛው አዋሽ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ የገናሌ ዳዋ እና የላይኛውና መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ከመደበኛው ጋር የሚቀራረብና ከወትሮው በላይ የሚጠበቅ ዝናብ አላቸው። የአዋሽና የምስራቃዊ ዓባይ  አዋሳኝ ተፋሰሶችና  በጥቂት የመካከለኛው  አዋሽ ፣ የላይኛው ተከዜና አፋር ደናክል  አዋሳኝ ከፍተኛ ቦታዎች በተሰወኑ ቦታዎቻቸው ላይ  አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል ሲል የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጄንሲ አስታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም