በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ማበረታቻ ይደረጋል- የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

129
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ማበረታቻ እንደሚደረግ ተገለፀ። የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ያዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር ዛሬ ተከፍቷል። የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ሲከፈት እንደተናገሩት "ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እድገት ወሳኝ የሆነው የባለሀብቶች ተሳትፎ በሚፈለገው መጠን አልጎለበተም"። በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ "ዝቅተኛ የሆነውን የባለሀብቶች ድርሻ ለማሳደግም ማበረታቻ ይደረጋል" ብለዋል። በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ሀገሪቷ በዘርፉ ካደጉ የዓለም ሀገራት ምድብ በቀዳሚነት እንድትመደብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ የሀገር ውስጥ በለሀብቶችን ማበረታታት የእቅዱ ዋና ትኩረት መሆኑንም ጠቁመዋል። የመስሪያ ቦታና ካፒታል እንዲሁም ልዩ የታክስ እፎይታ ህጎች እየተዘጋጁ በመሆኑ ማበረታቻው በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ  ዘርፍ የሚሰማሩ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋልም ብለዋል። የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ በበኩላቸው እስካሁን በነበረው ሂደት የኢንዱስትሪ  የድጋፍ ማዕቀፍ በመተግበሩ በተለይም "ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘርፉ እድገት አስመዝግቧል"። 150 አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች እንዲሳተፉበት በተዘጋጀው በዚሁ ኤግዚቢሽንና ባዘር የ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ለማከናወን መታቀዱንም ተናግረዋል። የተለያዩ ምርቶችን ይዘው የቀረቡ ተሳታፊዎችም በኤግዚቢሺኑ በመሳተፋቸው ብዙ ነገር እንደሚያተርፉ በመግለጽ በተለይም "ከሌሎች ተሞክሮ ለመውሰድ እንደሚጠቀሙበት" ተናግረዋል። ከሰኔ 5 እስከ ሰኔ 10 በሚቆየው የ 2010 በጀት ዓመት ሁለተኛው ዙር ሀገር አቀፍና አለማቀፍ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ኤግዚቢሽንና ባዛር የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ የዘርፉ ችግሮችን ለመለየትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያለመ ነው። ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተመረጡ  ከ130 በላይ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበትን  ኤግዚቢሽንና ባዛር  ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎም ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም