በምእራብ ሸዋ 3 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ተተከለ

99
አምቦ ኢዜአ ሐምሌ 24 / 2011  በምዕራብ ሸዋ ዞን በተያዘው የክረምት ወቅት ከ3 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች መተከላቸውን የዞኑ እርሻ፣ ቡናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡ ከሰብል በተጓዳኝ  ቡና በማልማት ገቢያቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ገልፀዋል ። በጽህፈት ቤቱ የቡና ልማት ኤክስቴንሽን ባለሙያ አቶ ገዛኸኝ ጀርመን ለኢዜአ እንደገለጹት ችግኞቹ  የተተከሉት በ722 ሔክታር የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ  ነው። ችግኞቹ በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ ዝርያዎች ናቸው። በዞኑ 11 ወረዳዎች የሚገኙ 10 ሺህ 621 አርሶ አደሮች በተከላው መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል ። የባኮ ቲቤ ወረዳ   አርሶአደር  በላቸው ተሰማ በሰጡት አስተያየት በባለሙያ ምክር በመታገዝ ያዘጋጇቸውን የቡና ችግኞች መትከላቸውን ተናግረዋል ። “በማሳዬ ውስጥ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጨመር ለችግኞቹ እንክብካቤ እያደረኩ ነው” ብለዋል። “ከዚህ ቀደም በተከልካቸው ችግኞች ፍሬ ለመስጠት እየደረሱ በመሆኑ በዘንድሮ ክረምት ልማቱን ለማስፋፋት ተጨማሪ ችግኞች ተክያለሁ” ያሉት ደግሞ የኖኖ ወረዳ  አርሶ አደር ቢቂላ ነሞምሳ ናቸው። የቡና ችግኞቹ የተከሏቸው ከሰብል ልማት በተጓዳኝ  መሆኑን አርሶ አደሮቹ አመልክተዋል። በምዕራብ ሸዋ  በቡና ተክል ከለማው 5 ሺህ 522 ሄክታር መሬት በየዓመቱ ከ7 ሺህ 500 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ  ከዞኑ እርሻ፣ ቡናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም