የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ ነው

147
ኢዜአ ሐምሌ 25 / 2011  የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት ገለጸ። የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር በ1978 የዓለም የተፈጥሮ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በፓርኩ ክልል ውስጥ በነበረው ልቅ ግጦሽ፣ በግብርና መስፋፋትና አቋርጦት በሚያልፈው መንገድ ምክንያት ፓርኩ እ.አ.አ በዩኔስኮ የአደጋ ተጋልጭነት ዝርዝር ውስጥ ተካቶ ነበር። ይህን ተከትሎ በመንግሥት በተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች ከሁለት ዓመት በፊት ከአደጋ ተጋላጭነት ዝርዝር ውስጥ ሊወጣ ችሏል። የፓርኩ ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳየው በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት በአገሪቱ የተካሄደውን ለውጥ ተከትሎ ፓርኩን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር ጨምሯል። በዚህም ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ገቢ መገኘቱ ነው የተገለጸው። በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ጥብቅ ቦታ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በአገሪቷ ከሚገኙ ፓርኮች ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ነው። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት ፓርኩን የሚጎበኙ ቱሪስቶች በዓመት በአማካይ 25 ሺህ የነበረ ሲሆን በአገሪቷ በታየው ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ለውጥ የጎብኚዎች ቁጥር ወደ 32 ሺህ ከፍ ብሏል። ''በፓርኩ ታሪክ ይህን ያህል ቱሪስት ጉብኝት ሲያደርግ የመጀመሪያው ነው'' ያሉት አቶ አበባው በ2011 ዓ.ም ዓመታዊ የፓርኩ ገቢ 36 ሚሊዮን ብር ሆኖ መመዝገቡን ተናግረዋል። ገቢው በቀጥታ በደረሰኝ የተቆረጠ መሆኑን ያብራሩት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ በተደራጀ መንገድ አገልግሎት የሚሰጡ ማህበራት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉም አስረድተዋል። የምግብ፣ የአስጎብኚ፣ የቱሪስት ደህንነት፣ የሆቴልና ሬስቶራንትና የዕቃ አከራይ ማህበራትንም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ጠቅሰዋል። ''የአገሪቷ ሠላምና መረጋጋት በተሻለ ሲረጋጋጥ ፓርኩን በዓመት 200 ሺህ የሚጠጉ ቱሪስቶች  እንደሚጎበኙት ይጠበቃል፤ ይህም ለአገሪቷና ለአካባቢው ማኀበረሰብ የተሻለ ገቢ ያስገኛል'' ብለዋል። እንደ አቶ አበባው ገለጻ የመሰረተ ልማት፣ የሆቴሎችና በአጠቃላይ የጎብኚዎችን ፍላጎቶች የሚያሟላ አቅርቦት እጥረት ከችግሮች መካከል ናቸው። በፓርኮች አካባቢ የቱሪስቱን ፍላጎት የሚያሟላ መሰረተ ልማት መገንባት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም የሚያሳድግ በመሆኑ 'በትኩረት ሊሰራበት ይገባል' ብለዋል። የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በበኩላቸው እንደገለጹት ፓርኩ ለመንግሥት ከሚያስገኘው ገቢ ባሻገር ለአካባቢው ማኀበረሰብ የስራ ዕድል እየፈጠረ ነው። ከፓርኩ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የአካባቢው ማህበረሰብ በየኔነት ስሜት እንዲንከባከበው ማድረግ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነና የማህበረሰቡን ግንዛቤ የሚያሰፉ ስራዎች ለማከናወን ውጥን መኖሩን አመልክተዋል። ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታትም ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ተናግረዋል። የፓርኩን የውስጥ አቅም ለመገንባት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የተናገሩት አቶ ኩመራ በተለይ ከፓርኩ አዋሳኝ ነዋሪዎች ጋር በቅርበት ለመስራት መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል። የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ 412 ኪሎ ሜትር ስኩዬር የቆዳ ስፋት ያለው ሲሆን ዋልያ፣ ጭላዳና ቀይ ቀበሮን ጨምሮ የበርካታ ብርቅዬ የዱር እንስሳት መኖሪያ ነው።                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም