የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተሞችን ለኑሮ ምቹ የማድረጉን ስራ በጥናት ሊደግፉት ይገባል ተባለ

50
ሐምሌ 25 / 2011 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተሞችን ለኑሮ ምቹ የማድረጉን ስራ በጥናት ሊደግፉት ይገባል ሲሉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም አሳሰቡ። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ፖሊሲ አውጪዎች በጥናት የሚመላከቱ መፍትሄዎችን በኃላፊነት በመውሰድ ገቢራዊ ማድረግ እንዳለባቸውም ተጠቁሟል። "ጥናትና ምርምር እንዲሁም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከተሞችን ለኑሮ ምቹ እናድርግ" በሚል ሃሳብ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባኤ ከተለያዩ የዓለም አገራት የመጡ የዘርፉ ተመራማሪዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ። የተለያዩ የዓለም ከተሞችን ልምድ በመቀመር ለፖሊሲ አውጪዎች መፍትሄ መጠቆም ደግሞ የጉባኤው ዋነኛ ዓላማ መሆኑ ተገልጿል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም የጉባኤው መክፈቻ ላይ "ከከተሞች ዕድገት ጋር ተያያዞ የሚፈጠሩ ችግሮች ካለ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር በዘላቂነት ሊፈቱ አይችሉም" ብለዋል። የኢትዮጵያ ከተሞች ከጥራት አንጻር በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው ያወሱት ሚኒስትሯ፤ እነዚህ ችግሮች በተጨባጭ መፍትሄ የሚያመጡ ሳይንሳዊ ጥናቶችን እንደሚሹ ገልጸዋል። በመሆኑም በየደረጃው የሚሰሩ ጥናቶች ለማህበረሰቡ ምን ለውጥ አምጥተዋል? በሚለው መመዘን አለባቸው ነው ያሉት። ከዚህ አንጻር ራሳቸው የሚመሩት ተቋም የከፍተኛ ትምህርት አሰራር ስርዓትን እንደገና ፈትሾ ማስተካከል እንደሚፈልግ በመጠቆም። የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነ መስቀል ጠና በበኩላቸው ጥናት መስራት ብቻ በራሱ ግብ ባለመሆኑ ባለድርሻ አካላት ለጥናቶች ገቢራዊነት ቁርጠኛ ሊሆኑ እንደሚገባ ይገልጻሉ። "በተለይ የፖሊሲ አውጪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ጥናቶችን አነፍንፈው በመውሰድ ሊጠቀሙባቸው ይገባል" ብለዋል። በከተሞች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በዩኒቨርሲቲዎች የሚጠኑ ጥናቶችን ገቢራዊ ማድረግ የሚያስችል ፖሊሲ ሊዘጋጅ እንደሚጋባ የተናገሩት ደግሞ በስዊድን አገር የስዊዲሽ ግብርና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ግርማ ወልደሰንበት ናቸው። ይህ እውን እንዲሆን የፐብሊክ ተቋማት ትልቁን ሚና ሊጫወቱ ይገባል ነው ያሉት። የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የአዲስ አበባ ከተማን ወደ ሜትሮፖሊታንነት ማደግ ተከትሎ ያሉባትን ችግሮች በጥናት በመፍታት ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የተቋቋመ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም