በትግራይ ክልል 21 ወረዳዎች የተከሰተውን ተምች ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው

141
መቐለ ሐምሌ 25/2011ዓ/ም ኢዜአ  በትግራይ ክልል በ21 ወረዳዎች በ3ሺህ 784 ሄክታር የተከሰተውን ተምች መቆጣጠሩን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡ ''የአፍሪካ ተምች'' በመባል የሚታወቀው ተባይ በ5ሺህ ሄክታር መሬት ያለውን የበቆሎና የማሽላ አዝርዕት ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ በቢሮው የአዝርዕት፣ዕፅዋት ተባዮች መከላከልና የኳራንታይን ደይሬክተር አቶ መብራህቶም ገብረኪዳን ለኢዜአ እንደገለጹት ተምቹን ባህላዊና ዘመናዊ መንገዶች ተከላክሏል፡፡ በዚህም ተባዩ ከተከሰተበት መሬት አብዛኛውን ለመቆጣጠር ቢቻልም የቁጥጥርና ክትትል ተገባራት መጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የመከላከል ሥራው ከጉልበት በላይ የደረሰ ቡቃያ በባህላዊ፣ ከጉልበት በታች ለሆኑት ደግሞ መድኃኒት በመርጨት እንደሚከናወን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። ሥራው ለአቅመ ደካማ አርሶ አደሮች ቅድሚያ በመስጠት በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ አቶ መብራህቶም ተናግረዋል፡፡ ተምቹ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በቀበሌዎች  በየቀኑ በቡቃያው ፍተሻ እየተደረጉ ሲሆን፣ ሥራው በግብረ ኃይል ደረጃ እንዲመራ ተደርገዋል ብለዋል፡፡ በቆላ ተምቤን ወረዳ ዓዲሓ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አብርሃ ተስፋይ በበኩላቸው በሁለት ሄክታር መሬት የማሽላ ማሳቸው ላይ ተባዩ በመታየቱ ወደ ኩታ ገጠም ማሳዎች እንዳይስፋፋ በባህላዊ ዘዴ  እየተከላከሉት መሆኑን ተናግረዋል። በጣንቋ አበርገለ ወረዳ ተከዘ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ትብለፅ መብራህቱ በግማሽ ሄክታር በሚገኘው ይዞታቸው ሰብሉ በመከሰቱ ከልጆቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ጋር ተባብረው በርበሬ በውሃ በጥብጠውና ደፍጥጠው እያጠፉት መሆኑን ገልጸዋል። አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም በመደራጀታችን በኅብረት አረም ለማረምና ተባይ ለመከላከል ረድቶናል ያሉት ደግሞ በቆላ ተምቤን ወረዳ የዓዲሓ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታፈረ ከበደ ናቸው። ተባዩ ሁሉንም ዓይነት አዝርዕት፣ቅጠላቅጠልና ሳር ስለሚያወድም ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል። ተባዩ በቆላ ተምቤን፣ ታሕታይ ቆራሮና አሕፈሮም ወረዳዎች መታየቱን ተናግረዋል። አርሶ አደሮች አካባቢያቸው በመዳሰስና ዕለታዊ ክትትል በማድረግ ለባለሙያችና ለግብረ ኃይሉ ማሳወቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል። በክልሉ በመኸር ወቅት አዝመራ 102ሺህ 292 ሄክታር በማሽላና 52ሺህ 794 ሄከታር በበቆሎ አዝርዕት መሸፈኑን የቢሮው መረጃ ያሳያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም