በወላይታ ዞን የ22 ሚሊዮን ብር የደን ልማት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

84
ኢዜአ ሀምሌ 25/2011 በወላይታ ዞን በኪንዶ ኮይሻ ወረዳ በአያያዝ ጉድለት ምክንያት የተራቆተው የባንቶ ተራራ ተከልሎ እንዲያገግም የሚያደርግ የ22 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ። በፕሮጀክቱ አተገባበርና ቀጣይ ውጤታማነት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሒዷል ። የዞኑ አከባቢ፤ደንና አየር ንብረት ለዉጥ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘለቀ ዛራ እንደገለፁት የዞኑ ህዝብ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ በማድረግ ከልምላሜያቸው ተጠቃሚ የመሆን የካበተ ልምድ አዳብሯል ። ከዚህ በፊት አሳታፊና አርሶ አደር ተኮር በሆነ መልኩ በሁምቦና ሶዶ ዙሪያ ወረዳዎች ከ4 ሺህ ሔክታር በላይ የተራቆተና የተጎዳ መሬት በመንከባከብ መልሶ እንዲያገግምና ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ እንደተቻለም አስረድተዋል። ከዚህ ውስጥም ባለፉት ሰባት ዓመታት 2ሺህ 800 ሔክታር መሬት በሚሸፍነው የሁምቦ የደን ልማት ፕሮጀክት የተከናወነው ስራ የመሬት ለምነትን በመመለስ የደረቁ ምንጮች እንደገና ፈልቀው ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደተቻለ ኃላፊው ተናግረዋል ። ልማቱን ወደ ካርቦን ሽያጭ ገበያ በማሳደግ የአካባቢውን ማህበረሰብ በኢኮኖሚ ረገድም ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑንም አቶ ዘለቀ ገልጸዋል። “የዞኑን የካበተ ልምድ በመቀመርም በኪንዶ ኮይሻ ወረዳ የሚገኝና ለከፍተኛ ጉዳት የተዳረገው የባንቶ ተራራን በሚቀጥሉት አራት ዓመታት መልሶ ለማልማት ወርልድ ቪዥን ከተባለ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የ22 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ተቀርፆ ይፋ ሆኗል”ብለዋል ። በፕሮጀክቱ እቅድ መሰረት በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በተራራውና በዙሪያው 800 ሔክታር መሬት ተከልሎ ከአካባቢዉ ስነ-ምህዳር ጋር የሚስማሙና ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ ሃገር በቀልና የውጭ ዝርያ ያላቸዉ ችግኞች እንደሚተከሉ አረጋግጠዋል። በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የስነ-ምግብና የአካባቢ ጥበቃ ክፍል ሃላፊ አቶ በኩረጽዮን አሳሳኸኝ በበኩላቸው እንደገለጹት አርሶ አደሩ፤መንግስትና የሚመለከታቸዉ አካላት በተቀናጀ መልኩ የአፈርና ዉሃ ጥበቃ ስራዎችን በመስራት ዉጤታማ መሆን እንደሚቻል በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተገኙ ተሞክሮዎች ማሳያ ናቸው። በዚህ መነሻም ድርጅቱ ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመሆን የማህበረሰቡን ፍላጎት፤የአጠባበቅ ስልትና ተሳትፎ በማጥናትና ተሞክሮውን በማስፋት ተጠቃሚ ለማድረግ ፕሮጀክቱ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል። ተራራው ሲከለል ለማገዶ፤ለከሰልና ለተለያዩ አገልግሎቶች እንጨት በመቁረጥ የሚተዳደሩ አርሶ አደሮችን በሌሎች የግብርና ስራዎች ፤በእንስሳት እርባታና መሰል ተግባራት በማሳተፍ የተተከለው ችግኝ ወደ ደንነት እንዲያድግ ለመጠበቅ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መመደቡን ተናግረዋል ። ተራራው ባለበት አካባቢ የሚገኘዉ የፈጨና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ያሲን ብርሃኑ በሰጡት አስተያየት ለበርካታ ዓመታት በዛፎች ተሸፍኖ የነበረዉ የባንቶ ተራራ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች በዙሪያው በሚኖሩ ግለሰቦች እየተጨፈጨፈ አሁን ላይ ባዶ እየሆነ መጥቷል። ተራራዉን ለመከለልና ለመጠበቅ በፕሮጀክት ደረጃ በተነሳው ሃሳብ ደስተኛ መሆናቸውን በመጠቆም ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል ። በፕሮጀክቱ አተገባበርና ቀጣይ ውጤታማነት ዙሪያ ትላንት በተካሔደው ምክክር ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ፣ የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም