በውሃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የሚታዩ የመረጃ አያያዝ ክፍተቶችን ማስተካከል እንደሚገባ ተመለከተ

65
አርባምንጭ ሰኔ 5/2010 ድህነትንና የምግብ ዋስትና ችግር  ለመቅረፍ  በውሃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የሚታዩ የቅንጅትና የመረጃ አያያዝ ክፍተቶችን  ማስተካከል እንደሚገባ  ተመለከተ። በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ በተካሄደው 18ኛው የዓለም አቀፍ የውሃ ሲምፖዚየም የተሳተፉት  በጀርመን የሙኒክ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር  ሉኬ ኦ ኦላንግ እንዳሉት  ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና  ሀገራት በውሃ ሀብት የታደሉ ናቸው፡፡ ሆኖም  ባላቸው የአስተዳደራዊና  የመረጃ ክፍተቶች ምክንያት  በሀብቱ በተገቢው  አልተጠቀሙም። በኢትዮጵያና በሌሎችም የቀጠናው ሀገራት ድህነትንና የምግብ ዋስትና ችግር በወሳኝ መልኩ ከስር መሰረቱ ለማስወገድ መንግስታት የውሃ አጠቃቀም አስተዳደርና መረጃ አያያዝ ክፍተቶችን በማስተካከል ማዘመን እንዳለባቸው  አመልክተዋል። ጥቂት ቢሆኑም በዘርፉ ሙያ የተሰማሩ ተመራማሪዎችን  ከፖሊሲ  አውጪዎች ጋር የሚያገናኝ ግልጽ አሰራር ሊኖር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የውሃ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ  ዳይሬክተር ዶክተር አብደላ ከማል በበኩላቸው ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንድትችል  በዘርፋ የምታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር ለማስወገድ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው በዘርፉ ያካበተውን ልምድ በመጠቀም በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ለመደገፍ በውሃ ላይ ብቻ የሚሰራ ተቋም ማደራጀቱን ጠቁመዋል። የውሃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ እንዳሉት መንግስት በዘርፋ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሳይንሳዊ መንገድ ማስወገድ የሚያስችል ምሁራንን ያካተተ  አሰራር እየዘረጋ ነው፡፡ ይህም ዩኒቨርስቲዎችን ከኢንዱስትሪዎችና ከምርምር ማዕከላት ጋር በማገናኘት ዘርፉን የማብቃትና የፖሊሲ ግብዓት ምንጭ የማድረግ ስትራቴጂ  እየተዘጋጀ  መሆኑን ገልጸዋል። ለሁለት ቀናት በተካሄደው ሲምፖዚየም ከ10 ዩኒቨርስቲዎችና ከተለያዩ ምርምር ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን በውሃው መስክ የተሰሩ የምርምር ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም