ኢቦላ  ከቁጥጥር ውጭ  ሊሆን  እንደሚችል  ኦክስፋም አስጠነቀቀ

61

ሐምሌ 25/2011 በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ከቁጥጥር ውጭ የመሆን አቅም እንዳለው ኦክስፋም አስጠንቅቋል።

ኦክስፋም ይህን ያለው ባለፈው ማክሰኞ ኢቦላ ለሁለተኛ ጊዜ በምስራቃዊ ጎማ ከተማ  እንደተከሰተ ሪፖርት መደረጉን ተከትሎ እንደሆነ ነው ቢቢሲ የዘገበው።

ማስጠንቀቂያው የተላለፈው የዴሞክራቲክ ኮንጎ መንግሥት አንድ በሽተኛ መሞቱን ማረጋገጡን ተከትሎ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ የሚገኘው የኦክስፋም የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር ኮርኔ ኤንዳው፤ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ሁከትና መፈናቀል ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶችን እያደናቀፈ መሆኑን በመግለጽ የንጹሁ ውሃ እና የአካባቢ ንጽህና ጉድለት ለበሽታው መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ እንዳለ መናገራቸውን መረጃው አትቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ሳምንት ኢቦላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ችግር መሆኑን ገልጾ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛውን የማንቂያ ደወል ሊሰማ እንደሚገባ ተጠቅሶ ነበር።

የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት ማስጠንቀቂያ ለአራተኛ ጊዜ መተላለፉና እ.ኤ.አ. ከ 2014 እስከ 2016 የምዕራብ አፍሪካን አንዳንድ ክፍሎች በኢቦላ ወረርሽኝ ከ 11ሺ 000 በላይ መሞታቸውን  ቢቢሲ አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም