አቤት ሆስፒታል ህክምናውን ለማስፋት የቦታ ጥበት እንቅፋት ሆኖብኛል አለ

123
ሀምሌ 24/2011( ኢዜአ) አቤት ሆስፒታል የቦታ ጥበት ህክምናውን በአቅሙ ልክ እንዳያስፋፋ እንቅፋት እንደሆነበት ገለጸ። ሆስፒታሉ ችግሩን ለመፍታት ከሌሎች ጤና ተቋማት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑንም ገልጿል። የሆስፒታሉ የህሙማን ፍሰትና የህክምና ጥራት ዳይሬክተር ዶክተር ሄኖክ ደረጄ ለኢዜአ እንዳሉት ሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የህሙማን ፍሰት እየጨመረ ነው። በ2010 ዓም በድንገተኛ ህክምና ክፍል አገልግሎት ያገኙ ህሙማን ቁጥር 10 ሺህ ሲሆን በተመላላሽ ደግሞ 15 ሺህ ሰዎች አገልግሎቱን ማግኘታቸውን አስታውቀዋል። በ2011 ዓ.ም ከ11 ሺህ በላይ የድንገተኛ ህክምና ታካሚዎችና ከ20 ሺህ በላይ ተመላላሽ ታካሚዎች ህክምና እንዳገኙም ተናግረዋል። ከድንገተኛ ታካሚዎች መካከል 50 በመቶ ወይም ከ 5 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑት በአደጋ የተጎዱ መሆናቸውን ጠቅሰው ከአደጋ ተጎጂዎች ውስጥ ሶስት ሺህ የሚደርሱ ወይም 48 በመቶ ያህሉ በመኪና አደጋ ተጎድተው ህክምና ያገኙ ናቸው ብለዋል። ከተመላላሽ ታካሚዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ በድንገተኛ ህክምና ስብራትና ሌላ ጉዳት ገጥሟቸው በቀጠሮ እንደታከሙና ከነዚህም በርካታዎቹ የአደጋ ታካሚዎች መሆናቸውን ዶክተር ሄኖክ ገልፀዋል። ይሁንና ሆስፒታሉ ባለበት የቦታ እጥረት ምክንያት ስራውን በሚፈልገው መጠን ለማስፋት አለመቻሉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ችግሩን ለመፍታት ከሌሎች የህክምና ተቋማት ጋር በመሆን በጥምረትና በዘመቻ መልክ ባለሙያዎችንና መሳሪያዎችን ወደተቋማቱ በመላክ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል። በቀጣይም ይህን ስራ ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። ሆስፒታሉ ግንባታ ለመጀመር የሚያስችል ቦታና በጀት በማግኘቱ የህንፃ ግንባታውን ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የአቤት ሆስፒታል የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ህክምና ኮሌጅ አካል ሲሆን በድንገተኛ አደጋ ለተጎዱ ህሙማን ህክምና እየሰጠ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም