የኢንዶኔዥያ አምባሳደር ለጉብኝት ደሴ ከተማ ገቡ

166
ሀምሌ 24/2011( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አልቡሽራ ባስኑር ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ዛሬ ደሴ ከተማ ገቡ ። አምባሳደሩ ኮምቦልቻ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የደሴ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ነጋዴዎችና ባለድርሻ አካላት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ የደሴ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ በላይነህ ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት አምባሳደሩ ወደ ደሴ  የመጡት የከተማ አስተዳደሩና ነጋዴዎች ባደረጉላቸው ጥሪ መሰረት ነው ፡፡ አምባሳደሩ በሁለት ቀናት ቆይታቸው ከደሴ ከተማ ባለሃብቶች፣ ነጋዴዎችና አመራሮች ጋር በኢንቨስትመንት፣ በወሎ ባህል፣ በንግድና በሌሎች ጉዳዮች ላይ  ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል ። የመምሪያው ኃላፊ እንዳሉት አምባሳደሩ የወሎንና  የአገራቸውን ባለሃብቶች በንግድ በማስተሳሰር የጋራ ጥቅም ለማሳደግ የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው ። በተለይ በቅርቡ የተቋቋመውን የአይጠየፍ አስመጪና ላኪ አክሲዮን ማህበር ለማበረታታት  የተለያዩ ምርቶች ወደ ኢንዱንዥያ የሚልክበት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ ብለዋል ። አምባሳደሩ በሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝታቸው በደሴ ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን ከጎበኙ በኋላ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም