በጋምቤላ ክልል ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በንቃት ለማሳተፍ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል–አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

103

ጋምቤላ  ሐምሌ 23/2011 በክረምት ወራት በሚካሄደው የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ውጤታማነት በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ወጣቱን በማሳተፍ በኩል በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ፡፡

በወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዙሪያ ለክልል፣ለዞንና ለወረዳ አመራሮችና ለወጣት አደረጃጀቶች በጋምቤላ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በክልሉ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የዘገየ ቢሆንም ሁሉም በትኩረት ከተሳተፈበት ከግብ ማድረስ ይቻላል።

ለዚህም በክልሉ ለሚካሄደው የወጣቶች የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳካት በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተለይም በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶችን በማስተባበርና ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳካት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ወጣቶች የሚሰጡት አገልግሎት ውጤታማ እንዲሆን መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ኡሞድ እንዳመለከቱት በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ የሚሆኑ ወጣቶችም እንደ ሀገር የተጀመረውን ለውጥ እውን ለማድረግና በተለይም እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ ልማት ለማሳካት ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡

የክልሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አጁሉ ኡቻር በበኩላቸው በተያዘው የክረምት ወራት በክልሉ እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች በክልሉ በሚገኙ በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ከዛሬ ጀምሮ ወደ ስራ ይገባሉ “ብለዋል ።

ወጣቶቹ  በትምህርት፣ በጤና ፣በአካባቢ ጽዳት፣በችግኝ ተከላ፣ በደም ልገሳና በሌሎችም የልማት ዘርፎች እንደሚሳተፉ በውይይት መድረኩ ላይ ከቀረበው ጽሑፍ መረዳት ተችሏል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በክልሉ እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚቆይም ተገልጿል፡፡