ኢትዮጵያ በችግኝ ተከላ የአለምን ክብረ ወሰን የያዘችበት ክስተት የህዝቦቿን አንድነት ማሳያና ስሟን ማደሻ ነው - ዲያስፖራዎች

53
ሀዋሳ (ኢዜአ)  ሐምሌ 23/2011 ኢትዮጵያ በችግኝ ተከላው የአለምን ክብረ ወሰን የያዘችበት ክስተት የህዝቦቿን አንድነት ማሳያና ስሟን ማደሻ ነው ሲሉ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገለጹ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት የተጀመረው "የአረንጓዴ አሻራ" ችግኝ ተከላ ፕሮጀክት የአገሪቷን የደን ሀብት ለማሳደግና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር ያለመ ነው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 በህንድ አገር 800ሺ በጎ ፈቃደኞች በአንድ ቀን 66 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የዓለም ክብረወሰን ይዘው እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ኢትዮጵያም ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት እስከ ምሽት 12፡00 ሰዓት ድረስ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር 353 ሚሊዮን 633 ሺ 660 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የዓለም ክብረወሰን መያዝ ችላለች። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ሪፖርት፤ የመሬት መንሸራተት፣ የአፈር ለምነት ማጣት፣ የደን መመንጠር፣ የብዝሃ ህይወት መመናመን፣ ድርቅ፣ ጎርፍ እና የአየር ብክለት ለአየር ንብረት ለውጡ መከሰት ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን ይጠቁማል። በኢትዮጵያም ይህንን ለመቆጣጠርና የደን ሃብትን ለማሳደግ በተደረገው የችግኝ ተከላ ዘመቻ ሁሉም ዜጋ አሻራውን በማሳረፍ በተከላው ተሳትፎውን አበርክቷል። በዚህም በመላ አገሪቷ በአንድ ጀንበር ለመትከል ከታቀደው 200 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ስኬት ማስመዝገብ ተችሏል። ይህም በተለይም "ኢትዮጵያዊ አንድነትን የማጠናከሪያ፣ ማህበራዊ ትስስርን መፍጠሪያ እነዲሁም ችግሮችን በጋራ የመፍታት ጥንካሬን ማሳያ ነው" ይላሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን። ላለፉት 38 ዓመታት ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ አትላንታ ጆርጂያ ያደረጉት ፕሮፌሰር ሰለሞን ነጋሽ እንደሚሉት፤ በአብሮነት መስራት ለአገርና ለህዝብ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና አለው። በተለይም ወጣቶችና ህብረተሰቡ የመተባበርና የመተጋገዝ ብሎም አንድ የመሆን ባህላችንን በማጎልበት አገሪቱን መጥቀም ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል። ከአሜሪካ መቅደስ አዳነ " አንደኛ በማህበረሰብ ሲታይ ማህበራዊ መስተጋብራችንን የሚያጠናክር በአንድ ላይ ከተባበርን በመትከል ብቻ ሳይሆን ሌላ አለም አቀፍ አቺቭመንትም ማድረግ እንችላለን"  ብለዋል። አገሪቷ አሁን ያስመዘገበችው ውጤትም በቀደሙት ጊዜያት በችግርና፣ በድህነት፣ በረሃብና በድርቅ ይነሳ የነበረውን ስሟን ዳግም በመልካም ጎኑ ለማደስ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ሲሉም ተናግረዋል። በአሜሪካ አትላንታ ጆርጂያ ነዋሪ ፕሮፌሰር ሰለሞን ነጋሽ እንዳሉት"በአንድ በኩል ኢትዮጵያ በአለም ዙሪያ አፍሪካ ሲባል ከችግር ጋር እንጂ ከጥሩ ነገር ጋር አይወሳም....... ለሁላችንም በአለም አቀፍ ደረጃ የሚጠቅም ነገር ነው።" የአሜሪካ ነዋሪ የሆኑት መቅደስ አዳነ " ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ፕሮፐርሊ በመጠቀም ደሃ ናቸው የሚለውንም ስም መለወጥ ይቻላል።" ኢትዮጵያ በአንድ ቀን  353 ሚሊዮን 633 ሺ 660 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ሪከርድ ያስመዘገበችበትን ሁነት የተለያዩ የውጭ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ቢቢሲ፣ ዘ ኔሽን፣ ሲኤን ኤን፣ አሶሼትድ ፕረስና ሌሎችም ይገኙበታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም