ኢትዮጵያ የኢቦላ ወረርሽኝ ቅድመ መከላከል ተግባሯን አጠናክራ ቀጥላለች

160

ሀምሌ 23/2011 (ኢዜአ) የኢቦላ ወረርሽኝን ለመከላከል ኢትዮጵያ ተገቢውን የቅድመ መከላከል ተግባር እያከናወነች ነው ሲል የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። የዓለም የጤና ድርጅት ሃምሌ 10 ቀን 2011 ዓ.ም በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንኮ ጎማ ከተማ የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ ተከትሎ በሽታው የዓለም አቀፍ የጤና ስጋት መሆኑን ማወጁ ይታወሳል።

በመሆኑም አገራት ወረርሽኙን ለመከላከል የቅድመ ዝግጅት ተግባራቸውን  እንዲያጠናክሩ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

ይህንን ተከትሎም ኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከል የቅድመ መከላከል ተግባሯን አጠናክራ መቀጠሏን  የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሳምንት ከሚያደርጋቸው 25 በረራዎች 7ቱ ወረርሽኙ ወደተቀሰቀሰባት ጎማ ከተማ የሚደረጉ ናቸው።

በመሆኑም ኢቦላ ወደኢትዮጵያ እንዳይገባ፤ ከገባም ወረርሽኙ ሳይቀሰቀስ ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅትና ቅድመ መከላከል ሥራ ተጀምሯል ብለዋል።

በዚህም መሰረት በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎችን በመለየትና የህክም አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የጤና ችግሩን ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ ገልፀዋል።

እንደ ምክትል ዳሬክተሩ ገለጻ በአዲስ አበባ ቦሌና የክልል አየር ማረፊያዎች፣ በእግረኛ ማቋረጫ ኬላዎችና ሌሎች ድንበር አካባቢዎች የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ነው።

ዝግጅቱ በሰው ኃይል፣ በለይቶ ማከሚያ ቦታዎችና መመርመሪያ መሳሪያዎች የሚከናወን መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ቦሌ፣ ድሬደዋ፣ መቀሌ እና ባህርዳር ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች በኩል ከተለያዩ አገራት የሚገቡ መንገደኞችን የሰውነት ሙቀት በመለካት የልየታ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የበሽታው ምልክት የሚታየው ከ2 እስከ 21 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ከጎንኮ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የሚመጡ መንገደኞች ከበሽታው ነጻ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚቆዩባቸው ጊዜያት እስከ 21 ቀናት ድረስ ባሉበት ቦታ ክትትል ይደረግላቸዋል ብለዋል።

ከአየር ማረፊያዎች በተጨማሪ በጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና ሌሎች ክልሎች ባሉ የእግረኛ ማቋረጫ ኬላዎች ላይ በሙቀት መለኪያ መሳሪያ የቅድመ ልየታ ተግባር እየተከናወነ ነው።

የበሽታው ምልክት የሚገኝባቸውን መንገደኞች ለመከታተል የሚያስችል የህክምና መስጫ ማዕከል መዘጋጀቱንም ምክትል ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

በመሆኑም በበሽታው የተጠረጠሩ፤ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቢገኙ ወደተዘጋጀው ህክምና መሰጫ ማዕከል ይወሰዳሉ።

በክልሎችም ተመሳሳይ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን በጋምቤላ ክልል አምስት ጊዜያዊ የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

በአየር ትራንስፖርት ከሚገቡ መንገደኞች በተጨማሪ በ18 የየብስ መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ የሰውነት ሙቀት በመለካት የልየታ ተግባር እየተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።

ኢንስቲትዩቱ ከ290 በላይ የህክምና፣ የህብረተሰብ ጤና እና ሌሎች አስፈላጊ ባለሙያዎችን ለቅድመ ዝግጅት ተግባር አሰማርቻለሁ ብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት  ኢቦላ የዓለም ጤና ስጋት እየሆነ መምጣቱን እንዲያውጅ ካደረጉት መካከል አንዱ ወረርሽኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሚኖሩባት ጎማ ከተማ መከሰቱ ነው።

ወረርሽኙ በከተሞች ላይ ሲከሰት ደግሞ ለመቆጣጠር አዳጋችና በቀላሉ ወደሌሎች ቦታዎች ሊተላለፍ ስለሚችልም ነው።

የኢቦላ ወረርሽኝ ኢቦላ በሚባል ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ገዳይ በሽታ ሲሆን ድንገት የሚጀምር ከፍተኛ ትኩሳት፣ የሰውነት መዛል፣ ተቅማጥና ትውከት፣  ሰውነት ላይ የሚወጣ ሽፍታና ሌሎች የበሽታው ምልክቶች ናቸው።

በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ደምና ከሰውነት በሚወጣ ሰገራ፣ ሽንት፣ አክታና ሌሎች ፈሳሾች እንዲሁም በሽተኛው ከተጠቀመባቸው ቁሳቁሶች ጋር በሚፈጠር ንክኪ ይተላለፋል።

እጅን መታጠብ፣ በበሽታው ከተጠረጠሩ ሰዎች ከሚወጡ ፈሳሾች ጋር ንክኪ አለማድረግና በኢቦላ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን ከመንካት በመቆጠብ በሽታውን መከላከል ይቻላል።

ህዝቡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የበሽታው ወረርሽኝ ባለመከሰቱ ስጋት እንዳይገባው የገለፀው ኢንስቲትዩቱ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ግን ተገቢ መሆኑን አሳስቧል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው የኮሌራ በሽታ 19 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ኢኒስቲትዩቱ አስታውቋል።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ሶስት ወረዳዎች አዲስ የኮሌራ በሽታ ከመከሰቱ ውጪ በሁሉም ክልሎች ስርጭቱን መቆጣጣር ተችሏል ነው ያለው ኢኒስቲትዩቱ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም