በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትና የኢንዱስትሪዎች ትስስር የሚጠበቀው ደረጃ ላይ አልደረሰም

66
ሀምሌ 23/2011 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትና የኢንዱስትሪዎች ትስስር የሚጠበቀው ደረጃ ላይ አለመድረሱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ። ሰልጣኞች የተማሩትን ወደ ተግባር ይቀይሩ ዘንድ ኢንዱስትሪዎች በእኔነት ስሜት ሊያስተናግዱ እንደሚገባ ነው ሚኒስቴሩ ጥሪ ያቀረበው። ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ልማት ጉባኤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እየተካሄደ ነው። ጉባኤው በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ኢትዮጵያ ያለችበት ደረጃ የሚዳስስ ሲሆን ያሉት ችግሮች ምንድን ናቸው? ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ምን ይመስላሉ? እንዲሁም በቀጣይ ምን ይደረግ የሚሉት ደግሞ የትኩረት አጀንዳዎች ናቸው። ምሁራን፣ ዘርፉን የሚመሩ ኃላፊዎች፣ የግሉ ዘርፍና ባለድርሻ አካላት በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ ነው። ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማሪያም በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ቴክኒክና ሙያ የአገሪቷ ኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆን ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው። ለዚህም ወደ ዘመናዊነት ሊሸጋገር ይገባል ነው ያሉት ፕሮፌሰሯ። ዘመኑ የቴክኖሎጂ አብዮት የፈነዳበት መሆኑን ጠቅሰው ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር መስራት እንደሚጠይቅም አንስተዋል። ያለውን የስራ ገበያ የሚመጥን ሰልጣኝ ማፍራትና በራሱ ስራ የሚፈጥር ተማሪን በመፍጠር በኩል በርከት ያሉ ችግሮች መኖራቸውንም  ይናገራሉ ሚኒስትሯ ። ጀርመንን የመሳሰሉ ያደጉ አገራት ከቴክኒክና ሙያ ብዙ መጠቀማቸውን ገልጸው ኢትዮጵያም እንደዚህ ዓይነት የተሞክሮና የልምድ ልውውጥ መድረክ ላይ መሳተፏ ለችግሮቿ  መፍትሄ ለማፈላለግ አይነተኛ ሚና አለው ሲሉም ተደምጠዋል። የቴክኒክና ሙያና  የኢንዱስትሪዎች ትስስር በጠንካራ መሰረት ላይ ካልተገነባ ውጤታማ መሆን እንዳማይቻል የሚገልጹት ፕሮፌሰር ሂሩት፤ አሁን ላይ ትስስሩ የሚፈለገው ደረጃ መድረስ አለማቻሉንም አልሸሸጉም። ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር አብዲዋሳ አብዱላሂ በበኩላቸው ኢንዱስትሪዎች ማህበራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመገንዘብ መንግሥትን ማገዝ አለባቸው የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። በጀርመን ተራድኦ ድርጅት/ ጂ አይ ዜድ/ የዘላቂ ስልጠናና የትምህርት መርሃ ግብር ኃላፊ ኖኮላ ደሚ እንደተናገሩት፤ በቴክኒክና ሙያ መስክ አገሪቷ ለውጥ እያመጣኝ ቢሆንም ለዘርፉ ያለው አመለካከት ዝቅተኛ መሆን ሰልጣኞች በሚጠበቀው ደረጃ እንዳይቀላቀሉ ማድረጉን መታዘባቸውን ይገልጻሉ። የግሉ ዘርፍና መንግሥት ተቀራርበው መስራት እንደሚኖርባቸው ያስገነዘቡት ኃላፊዋ፤ በተለይም በስልጠና መመሪያ ዝግጀት፣ በስልጠና መሳሪያ አቅርቦትና መርሃ ግብሮች ላይ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍም ትኩረት ይሻል ብለዋል። የጀርመን መንግሥት በኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ እንዲጎለብት ላለፉት ሀያ ዓመታት ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው  በቀጣይም የሚሰጠውን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም