በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ156 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ጤፍ በኩታ ገጠም ለማልማት እየተሰራ ነው

100
ሀምሌ 23/2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን በተያዘው የመኽር ወቅት ከ156 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ጤፍን በኩታ ገጠም ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የሰብል ልማት ሥራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ እምቢአለ አለኽኝ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በምርት ዘመኑ የጤፍን ምርታማነት ለማሳደግ አርሶ አደሩ በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲያለማ እየተደረገ ነው ። በዞኑ ዘንድሮ አጠቃል ከሚለመው ከ640 ሺህ ሄክታር ማሳ ውስጥ 200 ሺህ ሄክታሩ በጤፍ እንደሚለማና ከዚህ ውስጥም አብዛኛው በኩታ ገጠም የሚለማ መሆኑን አመልክተዋል። እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም 22 ሺህ ሄክታር የጤፍ ማሳ በኩታ ገጠም ለማልማት በዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል፡፡ አቶ እምቢአለ እንዳሉት ለአርሶ አደሮች በተደራጀ አግባብ የባለሙያ ድጋፍ በመስጠት በመስመር እንዲዘሩ እንዲሁም ሳይንሳዊ አሰራርን ተከትለው ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው፡፡ በኩታ ገጠም ማልማት አርሶ አደሩ በተደራጀ አግባብ ቴክኖሎጂን እንዲጠቀም ከማስቻሉም በላይ የሰብልተባይንና መሰል ችግሮችን በጋራ ለመከላከል ያግዘዋል፡፡ ከተሳታፊዎች መካከል የእናርጅ እናውጋ ወረዳ ጣሞ ደዋሮ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አማረ አበባው እንዳሉት ጤፍን በመስመርና በኩታ ገጠም መዝራታቸው ለምርታማነት ጠቀሜታ እንዳለው ካለፉት ጥቂት ዓመታት ልምዳቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል። “በመስመር መዝራት ከጀመርኩ ከሁለት ዓመት ወዲህ የዘር ብክነት ሳይኖር ከሩብ ሄክታር ማሳ የማገኘውን የምርት መጠን ከሦስት ወደ አምስት ኩንታል ማሳደግ ችያለሁ።” ብለዋል። በኩታ ገጠም የማልማት ሥራው ለአረም ቁጥጥርም ሆነ ለምርት አሰባሰብ ከፍተኛ እገዛ እደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል። ዘንድሮ ግማሽ ሄክታር የጤፍ ማሳ በኩታ ገጠም ለማልማት የዘር ሥራ ማከናወናቸውን ገልጸው፣ በግብርና ባለሙያ ታግዘው ካለሙት ማሳ ጥሩ ምርት እንደሚጠብቁ አስረድተዋል። “ጤፍን በኩታ ገጠም በመስመር እየዘራሁ ማልማት ከጀመርኩ ወዲህ ውጤታማ ሁኛለሁ” ያሉት ደግሞ በእዚሁ ወረዳ የመጠያ ቀበሌ ነዋሪ ቄስ ቢያድገህ አይተህ ናቸው። ከዚህ ቀደም በብተና ይዘሩ በነበረበት ወቅት ዘር ከማባከናቸው በተጨማሪ በሄክታር የሚያገኙት ከ12 ኩንታል ይበልጥ እንዳልነበር ጠቅሰዋል፡፡ “የግብርና ቴክኖሎጂን ተጠቅሜ  በኩታ ገጠም ማልማት ከጀመርኩ ወዲህ እጥፍ ምርት ማግኘት ችያለሁ” ብለዋል። ዘንድሮ ከእዚህ የተሻለ ምርት ለማግኘት ከአንድ ሄክታር በላይ ማሳ በኩታ ገጠም እያለሙ መሆናቸውንም አስረድተዋል ። በዞኑ በ2011/2012 የመኽር እርሻ በአጠቃላይ እየለማ ካለው መሬት ከ22 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም