ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ ተዓምር መፍጠር እንደሚችሉ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ማሳያ ነው

43
ሀምሌ 23/2011 ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ ተዓምር መፍጠር እንደሚችሉ የሐምሌ 22ቱ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማሳያ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገለጹ። ኢትዮጵያ 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር ለመትከል መርሃ ግብር ነድፋ ተግባራዊ በማድረግ እቅዷን ትናንት እውን አድርጋለች። በዚህም ኢትዮጵያ በህንድ አገር ተይዞ የነበረውን 66 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ቀን የመትከል የዓለም ሪከርድ ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል ሪከርዱን በአምስት እጥፍ ማሻሻል ችላለች። በአንድ ጀንበር ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ሲተከል ኅብረተሰቡ ያለማንም ጉትጎታ በራሱ ተነሳሽነት የተሳተፈበት እንደሆነም ነዋሪዎች ይናገራሉ። በአዲስ አበባ በችግኝ ተከላ የተሳተፉ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ "ዜጎቿ በአገራቸው ኢትዮጵያ አንድነት ላይ ድርድር አያውቁም"። የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት መቶ አለቃ ሸዋንግዛው አክሊሉ "በአድዋ ጦርነት ወቅት የታየው የኢትዮጵያውያን ትብብር ዛሬ በአረንጓዴ ልማት ተደግሟል" ብለዋል። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የጀመረችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ እውን ማድረግ የሚያስችል ገድልም ፈጽማለች ብለዋል። የቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ገዛኽኝ ክብረት በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራው ቀን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር "ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ ተዓምር መፍጠር እንደሚችሉ" ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል። "ኢትዮጵያውያን የምንታወቅበት የአንድነት፣ የመተባበርና የመተጋገዝ ባህላችን ዳግም በተግባር የታየበት ነው" ሲሉም ተደምጠዋል። የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ኤፍሬም መኮንንም ኅብረተሰቡ አገር አቀፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያለማንም ጎትጓች በራሱ ተነሳሽነት የሚሳተፍ መሆኑን አሳይቷል ብለዋል። በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ህፃናት፣ እናቶች፣ አዛውንቶች፣ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ወታደሮች በጋራ የተሳተፉትም ለሀገራዊ ጉዳይ ጽኑ አቋም ስላላቸው መሆኑንም ገልጸዋል። "በየትኛውም ሀገር ልዩነቶች ይኖራሉ" ያሉት አቶ ኤፍሬም፤ ልዩነቶችን ለመፍታት ግን "አንዱን ጠቅሞ ሌላውን የማይጎዳ፤ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሀገራዊ ዘመቻ መፍጠር ይገባል" ብለዋል። የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴ አገር ለማስረከብ ብሎም በዜጎች መካከል የአንድነት መንፈስን ለማላበስ ያግዛል፤ በመሆኑም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም