የ“አረንጓዴ አሻራ” ስኬትና የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዕይታ

74
ኢትዮዽያውያን የአገራቸውን ጥሪ በደስታ ተቀብለው በነቂሰ በመውጣት አረንጋዴ አሻራቸውን ለማስቀመጥ  በትናትናው ዕለት ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓም ታሪካዊ ገድል መጎናጸፋቸው ይታወቃል። ይህ የአረንጋዴ አሻራ ዘመቻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ዘመቻ በዕቅድ ደረጃ ከተያዘው በበለጠ ከ353 ሚሊዮን ችግኞች በላይ ተተክለዋል።  ይህን ተከትሎ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ታሪካዊ ስኬቱን እንዴት እንዳስትናገዱት እንደሚከተለው ተዳሷል። ከመገናኛ ብዙሃኑ መካከል ቢቢሲ አማርኛው ጉዳዩን በማስመልከት ዘገባ ሲያወጣ የቀደመው አልነበረም። ዘገባው ሀሳቡን ሲጀምር ኢትዮዽያ መላ ዜጎቿን በማስተባበር በህንድ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ሰበረች በማለት ገልጾ፤ በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  ዐብይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ለማስቀመጥ በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ሀሳብ ከዕቅዱ በላይ በመሄድ በህንድ በአንድ ቀን 66 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል በአለም አቀፉ ድንቃድንቅ መዝገብ “ቡክ ኦፍ ሪከርድስ” የተመዘገበውን የሰበረ ክስተት ነበር በማለት ሀሳቡን ያትታል። ዘገባው ሲቀጥል፤ በተባበሩት መንግስታት አየር ንብረት ሪፖርት በሚሊኒየም መባቻ ዋዜማ የአገሪቷ የደን ሽፋን 35 በመቶ እንደነበር አስታሶ፤ ከአመታት በኋላ ወደ 4 በመቶ ማሽቆልቆሉን አውስቷል።  ይህ ስኬት የመጣው ይላል ቢቢሲ በዘገባው የአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን በትብብርና መናበብ መስራት መቻላቸውን ህዝቡን ለመቀስቀስ የተጠቀሙበትን አኳሃን አሞግሷል። በመጨረሻም መገናኛ ብዙሃኑ ሀሳቡን ሲያጠቃልል ይህ  በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደው አረንጓዴ አሻራ በአገሪቷ በሰሞኑ አንዳንድ አካባቢዎች እየታየ የነበረውን ግጭትና አለመረጋጋት  ከማረጋጋቱም በላይ አሁን እየተስተዋለ ያለውን አላስፈላጊ ግጭትና ጥላቻን የማስቀረት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ታምኖበታል በማለት ሀሳቡን ቋጭቷል። “ኢትዮዽያውያን በአንድ ጀምበር 353 ሚሊዮን ችግኝ ተከሉ” በማለት ሀሳቡን የጀመረው ሌላኛው መገናኛ ብዙሃን ደግሞ የእንግሊዙ ታዋቂ ጋዜጣ ዘ ኢንዲፐንደንት ነው። ዘገባው  ሀተታውን ሲቀጥል የደን ሽፋኑ በአደገኛ ሁኔታ በእርሻ መሬት ጥበት ምክንያት በገፍ በሚካሄደው ጭፍጨፋ እያሽቆለቆለ የመጣውን የደን ሽፋን እንዲያገግም ዘመቻው አስቻይ ሁኔታዎችን ከመፍጠሩም በላይ የአገሪቷን ዜጎች ወደ አንድነት ያሰባሰበ ነው ሲል ይታውን ያስቀምጣል። ዘገባው ሲቀጥል አለም አቀፉን ክብረ ወሰን ለማሻሻል ባይሰራም ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተሰራው ስራ ዕጅግ አመርቂ እንደነበር ገልጿል። ታዋቂው እና አንጋፋው የአሜሪካ የዜና ምንጭ ሲ ኤን ኤን በአፍሪካ አምዱ ዘገባውን ሲጀምር “የአገሪቷ ዜጎች በነቂስ ወጥቶ ከ353 ሚሊዮን ችግኞችን በ12 ሰዓት ተከሉ” በማለት ዘግቧል። ዘገባው ሲቀጥል ክበረ ወሰኑን ለመስበር ዕኩለ ቀን ያልወሰደ እንደሆነ በማውሳት ከልጅ እስከ አዋቂ ችግኞችን በመትከል አንድነታቸውን ያሳዩበት ተግባር ነበር ሲል ሀሳቡን ያስቀምጣል። በአፍሪካ በህዝብ ብዛት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘዋ ኢትዮዽያ በአሁኑ ወቅት በአየር ንብረት ለወጥ ምክንያት ከህዝቦቿ መካከል አብዛኛው ቁጥር በግብርና እንደመተዳደሩ መጠን በአፈር መሸርሸር ምክንያት በአገሪቷ ለም መሬት በመጥፋት ላይ እንደሆነ በማስታወስ፤ ይህንን ጥልቅ አገራዊ ችግር ለመቅረፍ ያለመ አሰራር ነበርም ሲል መገናኛ ብዙሃኑ ዘግቧል። በመጨረሻም እኒህ የተተከሉት ችግኞች በአለም አቀፍ ደረጃ በአመት 10 ቢሊዮን የሚሆነውን የካርቦን ልቀት የመቀነስ አቅም እንዳለውም ሲ ኤን ኤን  ገልጿል። ታዋቂው ዘጋርዲያን በበኩሉ ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን በማውሳት ዘገባውን የጀመረ ሲሆን  “ዜጎች በዚህ በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ እያጋጠመ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ በመጋፈጥ አገሪቷ የተየያዘችውን ድህነትን የመቀነስ ዕቅድ ያጎለብታል”  በማለት ዘግቧል። በዶክተር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት በተያዘው ክረምት 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተያዘን ዕቅድ ለማሳካት ደግሞ በነፍስ ወከፍ 40 ችግኞችን መትከል አረንጓዴ ኢትዮዽያን መፍጠር እንደሚቻል ያሳየ አገራዊ ክስተት ነው ሲል ሀሳቡን ያስቀምጣል። በመጨረሻም ይህ በዕውነት መሳጭ የሆነ  አንድነትን መሰረት ያደረገ አካሄድ በረጅም እና አጭር ጊዜ የተያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ በማድረግ ትክክልኛውን ተክል በትክክልኛው ቦታ በመትከል እያንዣበበ የመጣውን የአየር ንብረት መለወጥ ከመቀነሱም በላይ ስነ ምህዳራዊ፤ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ነው ሲል  ዘጋርዲያን  በዘገባው አስፍሯል። “በርሃማዋ አገር ኢትዮዽያ በአንድ ጀምበር ከ353 ሚሊዮን ችግኞችን ተከለች” በሚል ሀሳቡን የጀመረው ደግሞ የአሜሪካው እንግሊዝኛው ድምጽ ነው። መገናኛ ብዙሃኑ በዘገባው ሀሳቡን ሲቀጥል በቀን 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተያዘው አገራዊ ዕቅድ ዘመቻ በደን መጨፍጨፍ ምክንያት እየመጣ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቀነስ ያሰበ መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህ ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ሪፖርት መሰረት በአሁኑ ወቅት 4 በመቶ ብቻ የሆነውን አገራዊ  የደን ሽፋን ቁጥሩን እንደሚያሳድገው ታምኖበታል ሲል ሀሳቡን ያስቀምጣል። የአውስትራሊያው መገናኛ ብዙሃን ስፔሻል ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኤስ ቢ ኤስ) በበኩሉ ኢትዮዽያውን የአየር ንብረት ለውጡን ለማስተካከል ያለመ አገራዊ ዘመቻ በማድረግ 350 ሚሊዮን ችግኞችን በላይ ተከሉ ሲል ዘገባውን የጀመረ ሲሆን መሰል ችግኞችን በመትከል እየተራቆተ የመጣውን የአፈር ለምነት ስጋት በመቀነስ በአፍሪካ ለኑሮ ምቹ የሆነች  አገር ለመፍጠር ያለመ አሰራር ነበር ሲል ሀሳቡን ቋጭቷል።   የሩሲያው ስፑቲኒክ ኢትዮዽያ ክብረ ወሰን መስበሯን በአመላከተበት ዘገባው ላይ ህንድ በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮኖች ዜጎችን  በማሳተፍ በ2017 66 ሚሊዮን ችግኞችን መትከሏን አውስቶ በኢትዽያ ግን ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጨምሮ በአገሪቷ የሚገኙ ሁሉም የማህበረሰብ አካል መሳተፋቸውን በዘገባው አውስቷል። ሌሎችም አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ማለትም ሚዲል ኢስት ሞኒተር፣ ሽንዋ፣ አፍሪካ ኒውስ እና የመሳሰሉት ጉዳዩን በግርምት የዘገቡበት  ክስተት ሆኖ አልፏል። በመጨረሻም በማህበራዊ  ትስስር ገጽ ሳይቀር የዕለቱ መነጋገሪያ የነበረው እና የተፈጥሮ አካል የሆነው ታማኙ ውሻ ዛፍን ለመትከል አንድ ችግኝ በአፉ ይዞ መታየቱ መነጋገሪያ ከመሆኑም በላይ ለአረንጓዴ አሻራ ዕቅድ ሁሉም እንደሚመለከተው ያመላከተ ክስተት ሆኖ አልፏል። ከዚህ በኋላም ቢሆን ችግኞችን መትከል ብቻም ሳይሆን የተተከሉትን በመንከባከብ እንዲጸድቁ ማድረግ ከመጪው መስከረም ጀምሮ ውሃ የማጠጣት እና የመንከባከብ  የሁላችን ሀለፊነት እንደሆነ የጠቀሱት ዶክተር አቢይ አህመድ፤ ይህንን ለማሳካት እና አገራዊ ንቅናቄ ከመፍጠር አንጻር አገራዊ አንድነትን ለማሳደግ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የየራሳቸውን አንግል ይዞ መሮጥ ብቻም ሳይሆን አንድ በሚያደርጉን አገራዊ አጀንዳዎችና ሀሳቦች ላይ በትብብር በመስራት አገራዊ ሀላፊነትን መወጣት እንዳለባቸው ያመላከተ ክስተት እንደነበረም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም