ከተማዋን ለሁለት የከፈለው ዋሻ መልሶ ለማገናኘት የተጀመረው የድልድይ ግንባታ መጓተት ቅሬታ አሳድሯል

81
ነቀምቴ ሰኔ 5/2010 በምስራቅ ወለጋ ዞን በኢባንቱ ወረዳ በዋሻ መደርመስ ምክንያት ለሁለት የተከፈለውን የህንዴ ከተማን መልሶ ለማገናኘት የተጀመረው የድልድይ ግንባታ በመጓተቱ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው በአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የድልድዩ ግንባታ በ2006 ዓ.ም ተጀምሮ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር። ሆኖም ግን ግንባታው እስካሁን ሳይጠናቀቅ መቆየቱን ያመለከቱት ነዋሪዎቹ የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ከነዋሪዎቹ መካካል ወይዘሮ የሹሜ መኮንን በሰጡት አስተያየት በዋሻው መደርመስ ምክንያት ከተማውን ለሁለት እንዲከፈል በማድረጉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታችንና በልማት ጥቅሞቻችን ላይ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው መሆኑን ተናግረዋል። ወይዘሮ የሹሜ እንዳሉት ችግሩ ባስከተለው ክፍተት ከፊሉ የከተማዋ ነዋሪ ህዝብ  በገበያ፣በጤና፣በትምህርትና በሌሎች አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ መሰናክል ፈጥሯል። በዋሻው ውስጥ ከአንዱ የከተማው ክፍል ወደ ሌላው ለመሄድ እስከ አስር ደቂቃ ብቻ ይወስድ የነበረው መንገድ  በዋሻው መደርመስ ምክንያት ከአንድ ሰዓት በላይ ለመጓዝ እንደሚገደዱም ጠቁመዋል። የድልድዩ  ግንባታ  ሲጀመር ችግራቸውን ይፈታል ብለው በተስፋ ቢጠብቁም በመጓተቱ  ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ጠቅሰዋል። አቶ ሁንዴ ገርቢ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው "ዋሻው መሰነጣጠቅ ሲጀምር አቤቱታ አቅርበን የነበረ ቢሆንም የአካባቢው መስተዳድር ከአቅሜ በላይ ነው በሚል ምክንያት ቸልተኝነት በማሳየቱ ለችግር ተጋልጠናል" ብለዋል። የኢባንቱ ወረዳ መንገዶች ባለስልጣን ኃላፊ  አቶ አብዲ በቀለ ስለጉዳዩ ተጠይቀው የግንባታው የውል ስምምነት በኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን እና በንጋት ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት መካከል በመፈጸሙ ወረዳው በክትትሉም ሆነ በቁጥጥሩ ሒደት ላይ የነበረው ተሳትፎ አናሳ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ሆኖ የህዝቡ ቅሬታ ለመፍታት ወረዳው እጁን አስገብቶ ግንባታው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ተባብረው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። 20 ሜትር ቁመትና 40 ሜትር ርዝመት የነበረውን የተደረመሰው ዋሻ ለመተካት የተጀመረው የድልድይ ግንባታ አሁን ላይ 95 በመቶ መድረሱንም አቶ አብዲ አስታውቀዋል። የንጋት ኮንስትራክሽን ባለቤት  አቶ አሰፋ ታሎሬ በበኩላቸው የድልድዩ ግንባታ መጓተት አምነው ቀደም ብሎ የተሰራው ዲዛይን ችግር የነበረበት በመሆኑ የማሻሻያ ስራው ተጨማሪ ስራና ወጪ በማስከተሉ እንደሆነ ገልጸዋል። በኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሃንድስ ኢንጅነር  ወንዱ ደሳለኝ በበኩላቸው ግንባታው የተጓተተው ከዲዛይን ለውጡ በተጨማሪ  ከውጪ የሚገቡ ብረታብረቶች ዋጋ መጨመርና የተቋራጩ አቅም ማነስ ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል። በ22 ሚሊዮን 900 ሺህ ብር ወጪ እየተገነባ ያለው ድልድዩ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ አጠናቅቆ ለማስረከብ ከተቋራጩ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም ኢንጅነሩ አመልክተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም