በጎንደር ከተማ ከ3 ሺህ በላይ የመትረየስ ጥይት ሲያዘዋውር የተገኘ ግለሰብ ተያዘ

74
ጎንደር ኢዜአ ሀምሌ 23/2011በጎንደር ከተማ ከ3 ሺህ በላይ የብሬል መትረየስ ጥይት በህገ-ወጥ መንገድ ሲያዘዋወር ተገኝቷል የተባለ ግለሰብ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ የከተማው ፖሊስ መምሪያው የህዝብ ግንኙነት ኦፊሰር ኮማንደር ማረልኝ ወንድም ለኢዜአ እንደተናገሩት ግለሰቡ የተያዘው ጥይቱን በከተማው ቀበሌ 16 ክልል በአንድ ባጃጅ በድብቅ ጭኖ ሲዘዋወር ነው፡፡ ህገ ወጥ ከሆነው ጥይቱ ጋር ሐምሌ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ አስር ሰዓት አካባቢ በድንገት በተካሄደ ፍተሻ ሊያዝ ችሏል፡፡ ጥይቱን ሲያዘዋውር የተገኘው ግለሰብ የባጃጅ አሽከርካሪም መሆኑን ኮማንደሩ አመልክተው በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን ገልጸዋል ። ከህገ-ወጥ የጥይት ዝውውሩ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለመያዝ ፖሊስ ተጨማሪ ክትትል እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ የጥፋት ኃይሎች በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያና ጥይት ዝውውር በመሳተፍ ሰላም እንዳያደፈርሱ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮማንደሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም