አረንጓዴው የጥንዶቹ ማስታወሻ

185

አዲስ አበባን እንደ ህፃን ልጅ አቅፎ በስስት ወደታች እየተመለከተ፣ ነዋሪዎቿ የበጋውን ፀሃይ ረስተው እፎይ እንዲሉ ቀዝቃዛ በረከቱን ‘እፍፍፍ’ እያለ መለገሱን የማይዘነጋው የእንጦጦ ተራራ ዛሬ ልዩ ግርማ ሞገስ ተላብሶ ነበር።

የከተማዋ ነዋሪዎች ተራራውን ባለበሰው አረንጓዴ የተፈጥሮ ልብስ ውስጥ በደስታ እየጨፈሩ የነገዎቹን ተስፋ ‘ችግኞች’ በእጃቸው አቅፈው ሽር ጉድ ሲሉ፤ ቀደም ብሎ የነበሩት የተራራው ዛፎች በያሬዳዊ ዝማሜ ደስታቸውን የተጋሯቸው ይመስላል።

ግማሾቹም  ለምለም ችግኞችን እንደ ካንጋሮ በደረታቸው ሳይቀር ታቅፈው በሳርና ቁጥቋጦ ጤዛ  በታጀበውና እግር በሚውጠው የክረምት ጭቃ ላይ በጀርባቸው ሲወድቁና ሲነሱ፤  የሚያሳዩት ልዩ ትርኢት አካባቢውን በሳቅ የሚያጅብ ድባብ አላብሶት ነበር።

ከሁሉም ግን በእጅጉ ቀልቤን የሳቡት ከ”አረንጓዴ አሻራ ቀን” የችግኝ ተከላ ድግስ ታዳሚዎች መካከል የተገኙት ጥንዶች ናቸው።

በርግጥም ጥንዶቹ ግርማ ታምራትና ትዕግስት ንጉሴ ተያይዘው ብዙ ጥንድ ዛፎችን ሲተክሉ ሚሊዮኖች ከተከሏቸው መቶ ሚሊዮኖች ችግኞች በላይ ለነሱ ትልቅ ትርጉም ነበረው።

አቶ ግርማን ስቀርበው ፊቱ ላይ ደስታና አንዳች ትዝታ ይነበብበት ነበር። ምክንያቱ ደግሞ እንዲህ ነው – ከአምስት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ በኩላሊት ህመም ሲሰቃይ ኖሯል።

እናም የዛሬ ሶስት ዓመት በዛሬዋ እለት ለአምስት ዓመታት የኖረበት የስቃይ ምእራፍ አክትሞ በደስታ የተለወጠበት ጊዜ መሆኑ ነው። በተደረገለት የኩላሊት ንቅለ ተከላ ዛሬ ጤነኛና የደስታ ህይወት መኖር ጀምሯል። በምንም ዓይነት ዋጋ የማይተመነውን ውድ ኩላሊቷን ለግሳ ህይወት የሆነችው ደግሞ የዛሬ የትዳር ተጓዳኙ ትእግስት ናት።

“ዛሬ የምተክላቸው ችግኞች አንድ ኩላሊቷን ለግሳ ህይወት ለሆነችኝ ሚስቴ ማስታወሻ ነው” ሲልም ነው ስሜቱን የገለፀው።

“ለኔ የተደረገልኝ ስጦታ በአፍ እሚወራ አይድለም እዚህ ጋር እንድገኝና ንፁህ አየር እንድተነፍስ የበቃሁት በሷ ምክነያት ነው ፣እሷ ባትኖር ኖሮ የለሁም ነበር ምናልባትም እዚህ ቦታ አልገኝም ነበር” ነው ያለው አቶ ግርማ ታምራት፡፡

“በቅድሚያ የማመሰግነው ፈጣሪያችንን ነው ለዚች ቀን ስላደረሰን እኔንጃ በቃ ታሪክ ነው ለዛሬው ቀን መብቃታችን ሁላችንም እግዚያብሄር ይመስገን” ወይዘሮ ትዕግስት ንጉሴ።

‘ለዚህ ታሪካዊ ቀን የበቃነው በፈጣሪ ቸርነትና በመተባበራችን ነው’ የሚሉት ጥንዶቹ ችግኞችን በመትከል ለሰዎች እስትንፋስን መለገስና ብዙ ህይወትን ማትረፍ እንደሚቻል በተግባር ለማሳየት እንደመጡም ይናገራሉ።

“ከህይወታችሁ ምን እንማር”? ለሚለው ጥያቄም ደግነት፣ ቅንነትና መተባበር የምንኖርባትን አለም መቀየር የሚያስችል አቅም አለው የሚል መልዕክታቸውን አጋርተውናል።

“ብዙ ሰዎች የተማሩት ነገር አለ በጎ ነገር ማድረግን፣ሰው ማድረግ እየቻለ……ለምሳሌ እኔ ገንዘብ ባይኖረኝ ኩላሊቴን ሰጥቼ ባለቤቴን አድኘዋለሁ፣ሌላም ሰው ገንዘብ ባይኖረው እንኳን ማድረግ የሚችለውን ለግሶ ለሰው ልጅ መለገስ በጣም ትልቅ ነገር ነው ስለዚህ ባለን ነገር ሁሉም ሰው ቢተባበርና በስቃይ ውስጥ ያሉ ሰዎች ቢረዳዱና መፍትሄ ቢያገኙ እላለሁ”።

“መተሳሰብ፣ መተባበር፣ ፍቅር፣ አብሮነት እና አንድነት ካለ የኢትዮጵያን ስኬትና ሃያልነት ማምጣት ይቻላል” የሚለው ሀሳብ የጥንዶቹ እምነት ነው።

ኢትዮጵያዊያን ለነገው ትውልድ ታሪክን ፅፈው ለሚያልፉበት ለዚህ የአረንጓዴ አሻራ ቀን በመድረሳቸው የተሰማቸውን ደስታም ገልፀዋል።