ኢትዮጵያውያን በችግኝ ተካላ ወቅት ያሳዩት ርብርብ የሚደነቅ ነው- ቆጠራውን የታዘቡ ዲፕሎማቶች

54
ሐምሌ 22 / 2011 ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀምበር በርካታ ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ያሳዩት ርብርብ የሚደነቅ መሆኑን የተከላውን ቆጠራ ሂደት የታዘቡ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦች ተናገሩ። በኢትዮጵያ ችግኝ ለመትከል የተወሰደው ኢንሼቲቭ አገሪቷ ለአረንጓዴ ልማት ያላትን አቋም የሚያሳይ መሆኑንም አክለዋል። ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ በሚል መሪ ሃሳብ በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የያዘቸውን ውጥን በ9 ሰዓታት ወስጥ ዛሬ ማሳካት ችላለች። ሁነቱም ከዚህ በፊት በአንድ ጀምበር 66 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል በህንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ሪከርድ ማሻሻል ያስቻለ መሆኑም ተገልጿል። የችግኝ ተካለ ቆጠራው በኮምፒዩተር በመታገዝ የታከሄደ ሲሆን፤ በአፍረካ ህብረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሴቶች ተወካይ ሊቴ ቺዋራ እና በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ዋግነር ሂደቱን በስፍራው በመገኘት ታዝበዋል። ሚስስ ሊቴ ቺዋራ በዚህን ወቅት ኢትዮጵያ በችግኝ ተከላው ላይ ያስመዘገበችው ስኬት እንዲሁ የተገኘ አለመሆኑን ገልጸው፤ በተለይ ሚዲያዎች ህዝብን በማንቃት በኩል ሰፊ ስራ መስራታቸውን እንደታዘቡ አውስተዋል። ኢትዮጵያውያን ከህጻን እስከ አረጋዊያን እድሜ ሳይገድባቸው ችግኝ ለመትከል ያሳዩት ቁርጠኝነትም እጅግ እንዳስደነቃቸውም አክለዋል። ይህም እለቱን ልዩ ቀን አድርጎታል ነው ያሉት። በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ዋግነር በበኩላቸው ዓለም ስለ አየር ንብረት ለውጥና ስለ ሙቀት መጨመር እየተጨነቀ ባለበት ወቅት እንዲዚህ አይነት ተግባር መከናወኑ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል። "ችግኝ ለመትከል በተንቀሳቀስኩበት ወቅት በርካታ ዜጎች በነቂስ ወጥተው ችግኝ ሲተክሉ ተመልክቻለሁ" ብለዋል። 'የዜጎች የአረንጓዴ አሻራ ቀን' በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ  ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ በተካሄደው አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ከ250 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን ከኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም