ዘላቂ ሰላምና ብሄራዊ መግባባት—በምሁራን አንደበት

3246

ምናሴ ያደሳ /ኢዜአ/

ለብሄራዊ መግባባትና አንድነት መጠናከር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና በሚል ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ሰሞኑን በመቱ ዩኒቨርስቲ ተካሔዷል፡፡ በጉባኤው ላይም ከሀገሪቱ የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተወጣጡ ከ300 በላይ ምሁራን በመስኩ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎቻቸውን አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

በጉባኤው ላይ የቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች ለብሄራዊ መግባባትና አንድነት መጠናከር ያሉትን መልካም እድሎችና ተግዳሮቶችን በመዘርዘር የመፍትሄ አቅጣጫ የጠቆሙ ናቸው ፡፡ ችግሮችን ለመቅረፍ የመንግስትና የመላው ህብረተሰብ ሚና ምን መሆን እንደሚገባውም ምሁራኑ ተወያይተውበታል፡፡

ለዘላቂ ልማትና እድገት የህገመንግስቱ ሚና በሚል የጥናት ስራቸውን ያቀረቡት በወለጋ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህር አቶ ሰለሞን ጥሩነህ እንዳመለከቱት በሀገሪቱ ለብሄራዊ መግባባት እና ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የኢፌድሪ ህገመንግስት ዋስትና ነው፡፡ ህገመንግስቱ በአንድ አካል ጸድቆ ተግባራዊ የተደረገ ሳይሆን ብሄር ብሄረሰቦች ተወያይተው ችግሮቻችንን ይቀርፍልናል በማለት በይሁንታቸው ያጸደቁት ህገመንግስት ነው ሲሉ አስምረውበታል፡፡

በህገመንግስቱ መግቢያ ላይ እንደሰፈረው “እኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሀገራችን  ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣  ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገታቸው እንዲፋጠን፣ የራሳችንን እድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነፃ ፍላጎታችን፣ በህግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን  በመነሳት” የሚለውን በመጥቀስ ይጀምራሉ።

ይህም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ብሄራዊ መግባባት እንዲሰፍን ህገመንግስቱ ተመራጭ  መሆኑን ያስረዳሉ። የኢፌዴሪ ህገመንግስት ከሌሎች ሀገራት ህገመንግስቶች በተለየ መልኩ ሁሉንም መብቶች አካቶ በመያዙ ዘመናዊና ለአፍሪካም በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

የኢፌዴሪ ህገመንግስት ከሌሎች ሀገራት ህገመንግስቶች በተለየ መልኩ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ የአካባቢያዊ ባህልን ጨምሮ ሁሉን መብቶች ያካተተና ለሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ዋስትና መሆኑን በጽሁፋቸው አመልክተዋል፡፡

የሀገሪቱ ህገመንግስትና የፌዴራሊዝም ስርአቱ ከሌሎች የአለም ሀገራት ጋር ሲነጻጸር በለጋ እድሜ ላይ እንደመገኘቱ በአፈጻጸሙ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በህገመንግስቱ ላይ በአንዳንድ አካላት ጥያቄ እንዲነሳ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት፡፡

በጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ እንዳመለከቱት የኢፌዴሪ ህገመንግስት ለኢኮኖሚያዊ እድገት ካልሆነ በስተቀር ሁሉንም መብቶች ያካተተ አይደለም በማለት እንዲሻሻል የሚጠይቁ አካላት ህገመንግስቱን በጥልቀት ካለመረዳትና አልፎ አልፎ የሚታዩትን ችግሮች የህገመንግስቱ ጉድለት አድርገው የሚወስዱት የተሳሳተ አተያይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሀገሪቱ አልፎ አልፎ የሚከሰቱት ችግሮች የሚመነጩት ህገመንግስቱን በአግባቡ ስራ ላይ ካለማዋል እና አፈጻጸሙን የሚከታተሉ የዲሞክራሲ ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ ካለመጠናከር እንጂ ከህገመንግስቱና ከፌዴራላዊ ስርአቱ ጉድለት እንዳልሆነ ተብራርቷል፡፡

በህገመንግስቱና በፌዴራላዊ ስርአቱ ዙሪያ የህብረተሰቡ እና የአስፈጻሚ አካላት የግንዛቤ ማነስ እንዳለ ሆኖ፡፡

በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ የሚገኙ አንዳንድ አዋጆችና ህጎችም ከ50 አመታት በፊት የወጡ በመሆናቸውና በፌዴራሊዝም ስርአቱ ስራ ላይ በሚውሉበት ወቅት በአፈጻፀም ሊታዩ የሚችሉ አንዳንድ ችግሮች እንዳሉ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ ለዚህም እንደ ወንጀለኛ መቅጫ እና የንግድ ህጎችን በመጥቀስ፡፡

በህገመንግስቱ አንቀጽ 92 መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንጹህና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው መጣር እንዳለበት እና ማንኛውም የኢኮኖሚ ልማት እርምጃ የአካባቢ ደህንነትን የሚያናጋ መሆን እንደሌለበት መደንገጉን አስታውሰዋል፡፡በመሆኑም የመንግስት አካላት ትላልቅ የልማት ፕሮጄክቶችን ሲያከናውኑ ጠለቅ ባለ ጥናት ላይ ተሞርኩዘው መሆን አለበት ይላሉ፡፡

የመንግስት አካላትም የዲሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር ለህገ መንግስታዊ መብቶች በአግባቡ መከበር ክትትል ማድረግና መስራት እንዳለባቸው በህገመንግስቱ ግዴታ ስለተጣለባቸው እነዚህን ተቋማት በደንብ ማጠናከር እንደሚገባም ነው የተመለከተው፡፡

ከነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የአፈጻጸም ችግሮች የተነሳ አልፎ አልፎ ግጭቶችና ያለመረጋጋቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል፡፡  የአፈጻጸም ችግሩን የፌዴራሊዝም ስርአቱና ህገመንግስቱ ነው በማለት አንዳንድ አካላት የሚሰጡት አስተያየት ችግሮቹንና የችግሮቹን መንስኤ ካለመረዳት የመጣ ነው ብለዋል፡፡

የኢፌዴሪ ህገመንግስት የብሄር ብሄረሰቦችን የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች የመለሰና ለመሰረታዊ መብቶቻቸው በተሟላ መልኩ መረጋገጥ ዋስትና ተደርጎ በይሁንታቸው በጋራ ያጸደቁት ነው፡፡  አፈጻጸሙን የሚከታተሉ የዲሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር በአግባቡ ስራ ላይ መዋላቸውን ማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ የሚገባ ጉዳይ መሆኑን በጥናቱ አስቀምጠዋል፡፡

በመቱ ዩኒቨርስቲ  የህግ መምህር አቶ ሙሉቀን ካሳሁን በሰጡኝ አስተያየት በአለም ላይ የፌዴራሊዝም ስርአት የሚከተሉ ሀገራት ከሀገራቸው ተጨባጭ ሁኔታና ፍላጎት በመነሳት ህገመንግስታቸውንና የፌዴራል ስርአታቸውን ያረቃሉ፡፡በምሳሌነት የጠቀሱት የአሜሪካ የፌዴራሊዝም ስርአት ከ200 አመታት በፊት ሲዋቀር በሀገሪቱ ያሉ 50 ግዛቶችን አንድ ላይ በማሰባሰብ በአለም ላይ በፖለቲካና ኢኮኖሚ ልዕለ ሀያል ለመሆን ካላት ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡እንደ ጀርመንና ብራዚል ያሉ ሀገራትም ለህዝቦቻቸው በቅርበት ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የፌዴራል ስርአታቸውን እንዳዋቀሩ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ ያጸደቁት የኢፌዴሪ ህገመንግስት እና የዘረጉት የፌዴራል ስርአትም ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታና ከብሄርብሄረሰቦችና ሀዝቦች  ፍላጎቶች መሰረት በማድረግ የተዋቀረ  ነው ይላሉ፡፡

በሀገሪቱ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ የብሄርብሄረሰብ የፖለቲካ ድርጅቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ አንግበው የተነሱት የማንነት ጥያቄ ነበር፡፡ በጋራ ያጸደቁት ህገመንግስታቸውም ይሄንኑ የማንነት ጥያቄያቸውን እንዲመልስ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት የየራሳቸው መንግስታዊ ተቋም እንዲመልስ በመደረጉ በሀገሪቱ ሰላም በማረጋገጥ በልማቱ ፊታቸውን እንዲያዞሩ እንዳደረገ ነው የተናገሩት፡፡

ህገመንግስቱ ለዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ዋስትና የሰጠ ቢሆንም በዋናነት በግንዛቤ ማነስ የተነሳ በአፈጻጸሙ ላይ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል፡፡ለዚህም ደግሞ የመንግስት አካላት አፈጻጸሙን እና አተገባሩን የሚከታተሉ የዲሞክራ ተቋማትን በማጠናከርና በዜጎች መሀል በህገመንግስቱ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖር በመስራት በህገመንግስቱ የተጣለባቸውን ግዴታ መወጣት እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡

ሌላኛው በጉባኤው ላይ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ያቀረቡት በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የግብርና ምጣኔ ሀብት መምህር ዶክተር አረጋ ሹመቴ በበኩላቸው ለአንድ ሀገር ሰላም እና ፖለቲካዊ መረጋጋት ጠንቅ ከሆኑት መካከል የሙስና እና ኪራይሰብሳቢነት በግንባር ቀደም  ይጠቀሳል፡፡ በሀገር ደረጃም ይሁን በተቋማት ውስጥ የሙስና እና ኪራይሰብሳቢነት  በጨመረ መጠን ፖለቲካዊ ያለመረጋጋት እና የሰላም መደፍረስ በዛው መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ አብራርተዋል፡፡

የሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት እንዳይፈጸሙ መከላከል ብቻ ሳይሆን አመለካከቱን የሚጸየፍ ትውልድ መቅረጽ ያስፈልጋል፡፡ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቁ ስነምግባር ያለው ዜጋ በመፍጠር ረገድ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

የመቱ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ገለታ መረራ በበኩላቸው በአንድ ሀገር ብሄራዊ መግባባቱን ለማጠናከርና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ምሁራን ያላቸውን ሚና በመረዳት በሀገሪቱ ለሚከናወኑ የሰላም ልማትና መልካም አስተዳደር ግንባታ ከዳር መድረስ በጥናትና ምርምር የታገዘ የመፍትሄ  ሀሳባቸውን በማቅረብ ይበልጥ ሊተጉ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡

የመቱ ዩኒቨርስቲ ባዘጋጀው ጉባኤም በሀገሪቱ ብሄራዊ መግባባትና አንድነትን ለማጠናከር  ያሉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶችን የዳሰሱ የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት ተካሄዶባቸዋል፡፡ የመቱ ዩኒቨርስቲ ከጥናትና ምርምር ጉባኤው የሚያገኛቸውን ግብአቶች በመቀመር በመማር ማስተማሩ፣ በጥናትና ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራት ከመቼውም በበለጠ መልኩ ጠንክሮ እንደሚሰራ ነው ፕሬዝደንቱ የገለጹት፡፡

የመቱ ዩኒቨርስቲ ባዘጋጀው በዚህ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ከሀገሪቱ የተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተወጣጡ ከ300 በላይ ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን 90 የጥናትና ምርምር ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡