ወጣቱ በኪነ ህንጻ ጥበብ የአባቶችን ፈለግ ተከትለው ለላቀ እድገት መንቀሳቀስ አለበት---የኢፌዴሪ ፕሬዘዳንት

70
ሐምሌ 22 ቀን 2011 (ኢዜአ ) ወጣቱ ትውልድ በኪነ ህንጻ ጥበብ ታላቅ የታሪክ አሻራ ጥለው ያለፉ አባቶችን ፈለግ በመከተል ለሀገር የላቀ እድገት በቁጭትና በእልህ መንቀሳቀስ እንዳለበት የኢፌዴሪ ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ፡፡ ፕሬዘዳንቷ በጎንደር ከተማ የሚገኘውን የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስትና የመዋኛ ስፍራ እንዲሁም የደብረ ብርሃን ስላሴ ጥንታዊ ቤተ-ክርስቲያንን ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱ ማብቂያ ፕሬዘዳንቱዋ “የጎንደር የነገስታት ኪነ ህንጻዎች የላቀ የኪነጥበብ መገለጫዎችና የቀደመው ስልጣኔያችን የታሪክ አሻራዎች ናቸው “ብለዋል፡፡ ይህን አስደናቂ ታሪክ የሰራ ህዝብ ሀገርን በማሳደግ የኢትዮጵያን የቀደመ ገናና ስሙዋን ለመመለስ የሚያግደው ነገር እንደማይኖር ገልጸው ተባብሮ በአንድነት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ያለፈን ታሪኩን የማያውቅ፤ ጥሩም ሆነ መጥፎ የማይጋፈጥ ህዝብ ርቀት ሊሄድ እንደማይቸል የተናገሩት ፕሬዚደንቷ “ታሪክን በአግባቡ በማወቅና በመዘከር ትውልዱ የራሱን ታሪክ በማሳረፍ የአባቶቹን ፈለግ ሊደግምና ሊከተል ይገባል” ብለዋል፡፡ ሀገርን ማሳደግና ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ የመንግስት ኃላፊነት ብቻ እንዳልሆነ አመልክተው መንግስት የመምራት ኃላፊነት ህዝብ ደግሞ በመደገፍ የድርሻውን መወጣት እንደለበት አስገንዝበዋል፡፡ የሀገሪቱ የአኩሪ ታሪክ ባለቤትና ጎንደርም የቀደመ ስልጣኔ አሻራ መገለጫ መሆኑዋን የተናገሩት ፕሬዘዳንቱዋ እነዚህን ታላላቅና ዘመን ተሸጋሪ ቅርሶችን ለቱሪዝም ዘርፍ በስፋት እንዲውሉ ማስተዋወቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የጎንደርን ታሪካዊና የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በታሪክ መጻህፍት በሚገባ እንደሚያውቁዋቸው ተናግረዋል። “እድሉን በማግኘት በአካል መጎብኘቴ እጅግ አስደስቶኛል “ብለዋል፡፡ ፕሬዘዳንቱዋ በተጨማሪም የጎንደር ዩንቨርሲቲንና የዩንቨርሲቲውን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጎበኙ ሲሆን በዩንቨርሲቲው የስራ ኃላፊዎችም ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡ በሀገሪቱ ዛሬ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ቀን ፕሬዘዳንቱዋ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ምንዝሮ በተባለው የገጠር ቀበሌ በመገኘት የችግኝ ተከላውን በማስጀመር አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ የፌደራል የክልል፣ የዞንና የጎንደር ከተማ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም