የግብርናና አጣና ምርት ሽያጭ ከ29 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ተገኘ

1047

መተማ ሰኔ 5/2010 በመተማ በኩል ወደ ሱዳን ከተላኩ የግብርናና አጣና ምርት ሽያጭ ከ29 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የመተማ ዮሃንስ ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያ አስታውቋል፡፡

በጣቢያው የወጭ እቃዎች ቡድን አስተባባሪ አቶ እሱባለው ገደፋው ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፉት 11 ወራት ወደ ሱዳን ከተላኩ ምርቶች የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ10 ነጥብ 14 ሚሊዮን ከእቅዱ ደግሞ በ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብልጫ አለው፡፡

ገቢው ሊያድግ የቻለውም በውጭ አገር የምርቱ ተፈላጊነት እያደገ መምጣቱና የገንዳውሃና የመተማ ዮሀንስ የነበሩ መቅረጫ ጣቢያዎችን  በማዋሀድ ቀልጣፋ አገልግሎት መሰጠት በመጀመሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ወደ ውጭ ከተላኩት የግብርና ምርቶች መካከል ባቄላ፣ ቅመማ ቅመም፣ ግብጦ ሲሆኑ አጣናም ሌላው ወደ ውጭ ከተላኩት መካከል እንደሆነ ታውቋል፡፡

አካባቢው ከፍተኛ የሰሊጥ ምርት የሚገኝበት ይሁን እንጅ በመቅረጫ ጣቢያው ሰሊጥ እንዳልተላከ የገለፁት አቶ እሱባለው የሰሊጥ ምርቱ በጅቡቲ በኩል እንደሚላክ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የደረቅ ወደብ ስራው ተጠናቆ አገልግሎት ሲጀምር የተሻለ የውጭ ምንዛሬ የሚገኝበት እንደሚሆን አቶ እሱባለው እምነታቸው ገልፀዋል፡፡

አስመጭና ላኪ የሆኑት አቶ አብርሃ ተስፋሁን እንደተናገሩት ”የመተማ ዮሐንስ መቅረጫ ጣቢያ ቀልጣፋ የጉምሩክ አሰራር ስለሚከተል በስራችን ውጤታማ ሆነን ራሳችንንና ሃገራችን እንድንጠቅም አግዞናል” ብለዋል፡፡

የአጣና ምርት ወደ ውጭ እንደሚልኩ የገለፁት አቶ አብርሃ በቀጣይ ሌሎች የግብርና ምርቶችን በመላክ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግና ራሳቸውንም ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ወደ ውጭ ሃገራት ከተላኩ ምርቶች 20 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ተገኝቶ እንደነበር  ታውቋል።