የአዳማ ከተማ የቅርጫት ኳስ ቡድን ተጫዋች ጂከም ፒተር ለሁለት ዓመት ታገደ

59
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 የአዳማ ከተማ የቅርጫት ኳስ ቡድን ተጫዋች የሆነው ጂከም ፒተር ባሳየው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ለሁለት ዓመት ከጨዋታ ታገደ። የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ የውድድር ባለሙያ አቶ  አብዱልፈታ ተማም ለኢዜአ እንዳሉት ተጫዋቹ እገዳው የተላለፈበት ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም  በራስ ኃይሉ ጅምናዚየም የካ ክፍለ ከተማና አዳማ ከተማ የኢትዮጰያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ  ጨዋታ ላይ ዳኛውን ገፍትሮ በመጣሉ ምክንያት ነው። በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ላይ ጂከም ፒተር የዳኛ ውሰኔ በመቃወም የዕለቱን ዋና ዳኛ ቢንያም ጽጌን ገፍትሮ መሬት ላይ መጣሉን የጨዋታው ኮሚሽነር ሪፖርት አቅርበዋል። በዚህም የተነሳ 37ኛ ደቂቃ ላይ የነበረው ጨዋታ ተቋርጧል ያሉት ባለሙያው በወቅቱም አዳማ ከተማ የካ ክፍለ ከተማን 51 ለ 31 እየመራ ነበር ብለዋል። የፌዴሬሽኑ የውድድርና ስነ-ስርአት ኮሚቴ የጨዋታውን ኮሚሽነር ሪፖርት በመገምገም ተጫዋቹ ዳኛ በመገፍተር የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት መፈጸሙ በመረጋገጡ በቅርጫት ኳስ ውድድሮች ላይ ለሁለት ዓመት እንዳይሳተፍ ቅጣት ማስተላለፉን አመልክተዋል። ከእገዳው ባሻገር ተጫዋቹ የሶስት ሺህ ብር ቅጣት የተላለፈበት ሲሆን የገንዘብ ቅጣቱን ቡድኑ እንዲከፍል ተወስኗል። ከዚህም ሌላ የየካ ክፍለ ከተማ  የቅርጫት ኳስ ቡድን ጨዋታው ከተቋረጠ በኋላ ጨዋታው 'ይቀጥል አይቀጥል' የሚለውን የዳኞች ውሳኔ ሳይሰሙ የመጫዋቻ ሜዳውን ለቀው በመውጣታቸው ጨዋታው ሲቋረጥ ተይዞ በነበረው የጨዋታው ውጤት መሰረት አዳማ ከተማ አሸናፊ እንዲሆንም ኮሚቴው መወሰኑን አቶ አብዱልፈታህ ገልጸዋል። በሁለቱም ጾታዎች የሚካሄደው የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የተጀመረው በ2006 ዓ.ም ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም