በውሃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የሚታዩ ችግሮች ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ

221
አርባምንጭ ሰኔ 6/ 2010 ድህነትን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት ለማፋጠን በውሃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የሚታዩ የቅንጅት፣ የመረጃ አያያዝና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ። የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር በበኩሉ ችግሮቹን ለማስወገድ ምሁራንን ያካተተ የአሰራር  ስርዓት ለመዘርጋት እየሠራሁ ነው ብሏል። በጀርመን የሙኒክ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር  ሉኬ ኦላንግ እንደተናገሩት ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ሰፊ የውሃ ሃብት አላቸው፡፡ ባላቸው አስተዳደራዊና የመረጃ ክፍተት ምክንያት ግን የውሃ ሃብታቸው በተገቢ መንገድ መጠቀም አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ ስር የሰደደ ድህነት የቀጠናው የጋራ ችግር መሆኑን የገለጹት ዶክተር ኦላንግ ችግሩን ከመሠረቱ ለማስወገድ መንግስት የውሃ አጠቃቀም፣ አስተዳደርና መረጃ አያያዝ ስርዓቱን ማዘመን እንዳለበት ጠቁመዋል። "በዘርፋ ከፍተኛ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ከመኖሩ በላይ ያሉት ጥቂት ተመራማሪዎችም ቢሆን ከፖሊስ አውጪዎች ጋር የሚያገናኝ ግልጽ አሰራር ባለመኖሩ ባለድርሻ አካላት እንዳይቀናጁ ማነቆ ሆኗል" ብለዋል፡፡ የአርባምንጭ ዩኒቨርሰቲ የውሃ ኢንስቲትዩት ሳይንትፊክ ዳይሬክተር ዶክተር አብደላ ከማል በበኩላቸው ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ "የአፍሪካ ማማ" ተብላ እንደምትጠራ ገልጸዋል። ሀገሪቱ ዓመቱን ሙሉ ከሚፈሱ ከ12 ትላልቅ ወንዞች ብቻ በዓመት 124 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር የገጸ ምድር ውሃ ቢኖራትም አብዛኛው ሀብት በስራ ላይ ሳይውል እየባከነ ነው፡፡ ''በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከ36 ቢሊዮን በላይ የከርሰምድርና ከ96 ቢሊዮን ኪውብክ ሜትር በላይ ከምንጮችና ሐይቆች የሚገኝ የውሃ ሃብት አላት'' ብለዋል። ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንድትችል በዘርፋ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት ማቃለል ወሳኝ ነው፡፡ ''የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል በማምረት የድርሻውን እየተወጣ ነው'' ብለዋል። ዩኒቨርስቲው በዘርፉ ያካበተውን ልምድ በመጠቀም በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ለመደገፍ በውሃ ላይ ብቻ የሚሰራ ተቋም ማደራጀቱን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን፣ መስኖ ዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ስራ ሂደት አስፈጻሚ ዶክተር ጥላሁን ደረሰ እንዳሉት ኢትዮጵያ በከርሰ ምድርና ገፀ ምድር ውሃ ሊለማ የሚችል ከ40 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የመስኖ መሬት አላት። ከዚህ ውስጥ "ስራ ላይ የዋለው 7 ነጥብ 5 ከመቶ የዘለለ አይደለም" ብለዋል። በተለይ ከርሰ ምድር ውሃ አጠቃቀም በከተሞች ለንፁህ መጠጥ ከመዋል ውጪ በገጠሩ አከባቢ ጥቅም ላይ አለመዋሉን ተናግረዋል። ከርሰ ምድር ውሃ በገጠሪቱ አከባቢ ጥቅም ላይ እንዳይውል የኤሌክትርክ ኃይልና ቴክኖሎጅ አለመስፋፋት ከፍተኛ ማነቆ መሆኑን ገልጸው መንግስት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል። የኢፌዴሪ ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሽ በቀለ በበኩላቸው እንዳሉት መንግስት በዘርፋ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሳይንሳዊ መንገድ ማስወገድ የሚያስችል አሰራር እየዘረጋ ነው። ይህም ዩኒቨርስቲዎችን ከኢንዱስትሪዎችና ከምርምር ማዕከላት ጋር በማገናኘት ዘርፉን የማብቃትና ፖሊሲ ግብዓት ምንጭ የማድረግ ሰትራቴጅ የመዘርጋት ስራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ላለፉት ሁለት ቀናት በተካሄደው ዓለም ዓቀፍ ውሃ ሰሞፖዚየም ከ10 ዩኒቨርቲዎችና ከተለያዩ ምርምር ተቋማት የተወጣጡ ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን 22 በውሃው መስክ የተሠሩ ምርምሮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም