ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ አድዋን የሚዘክር ሩጫ ይካሄዳል

64
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ የአድዋ ድልን የሚዘክር የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል። ውድድሩን የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፤ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ የሚያዘጋጁት ነው። የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጻነት ታከለ ለኢዜአ እንደገለጹት ውድድሩ የሚካሄደው አርበኞች በአድዋ ድል ያስመዘገቡትን ድልና የከፈሉትን መስዋዕትነት ለመዘከር ነው። የመጀመሪያው ውድድር 123ኛው የአድዋ ድል በዓል የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ.ም "ኑ ለኢትዮጵያና አፍሪካ የአድዋ ድል የነጻነት ተምሳሌት እንሩጥ" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ተናግረዋል። በውድድሩ ላይ አትሌቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሮጡ ገልጸው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ኮሚቴዎች ተደራጅተው እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው ብለዋል። ጀግኖች አርበኞች በአድዋ አኩሪ ታሪክ እንደፈጸሙት ሁሉ አትሌቶችም በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች አገራቸውን በማስጠራት የስፖርቱ አርበኛ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል። በውድድሩ ላይ የአድዋን ድል የተመለከቱ መልዕክቶች ለማስተላለፍ እንዲሁም ህብረተሰቡ በሩጫው ላይ እንዲሳተፍ የንቅናቄ ስራ ለማከናወን ዕቅድ መያዙን ነው አቶ ነጻነት ያስረዱት። የአድዋን ድል የሚዘክረው የጎዳና ላይ ሩጫ ቀጣይ ዓመት የሚጀመርና በየዓመቱ በቋሚነት የሚካሄድ ውድድር መሆኑን አስታውቀዋል። ውድድሩን ለሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎች ከሚሰጠው የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት በተጨማሪ ፌዴሬሽኑ ለጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል። የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአድዋው የሩጫ ውድድር በተጨማሪ መስከረም 2011 ዓ.ም የሰንደቅ ዓላማ ቀንን በማስመልከት የ10 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ እንደሚያካሂድም ጠቁመዋል። በሐምሌ 2010 ዓ.ም ኑ ለአዲስ አበባ ከተማ አትሌቲክስ ዕድገት እንሩጥ በሚል የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ እንደሚካሄድና ውድድሩ የሚካሄድበት ቀን ፌዴሬሽኑ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚያሳውቅም ነው አቶ ነጻነት የገለጹት። በአጠቃላይ ውድድሮቹ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት፣ በመዲናዋ በአትሌቲክስ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክቶች የሚታቀፉ ተወዳዳሪዎችን ለመመልመልና በከተማዋ የአትሌቲክስ ስፖርት እንዲስፋፋ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አክለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም