የጋምቤላ ክልል ለ2012 በጀት ዓመት ከሁለት ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ

50
ጋምቤላ ኢዜአ ሐምሌ 21 /2011 የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለ2012 የበጀት ዓመት የልማት እቅድ ማስፈፀሚያ ከሁለት ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት፣ዓዋጆችንና ሹመት በማጽደቅ ተጠናቀቀ። የክልሉን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳዳር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በአዲሱ በጀት ዓመት ባለድርሻ አካላት እንዲሰሩ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አሳስበዋል። ጉባዔው በሁለት ቀናት ቆይታው በክልሉ በ2011 እቅድ አፈፃፀም ላይ ከመከረ በኋላ የ2012 በጀት ዓመት የልማትና መልካም አስተዳደር ግቦችን ለማሳካት ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጽድቋል፡፡ ከጸደቀው በጀት መካከል 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ለክልል መንግሥት፣ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ፣ ለመደበኛና ለመጠባበቂያ ተመድቧል። ቀሪው ለዞንና ለወረዳዎች እንደተመደበ ተብራርቷል። የጸደቀው በጀት ከክልሉ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች፣ከፌደራል መንግሥት ድጎማ እንዲሁም ከውጭ ብድርና እርዳታ እንደሚሸፈንም ተመልክቷል፡፡ በክልሉ የጸደቀው በጀት ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ251 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለውም ተገልጿል። ምክር ቤቱ ሁለት የተሻሻሉ ዓዋጆችንና የ14 በዞንና በወረዳ ደረጃ የሚያገለግሉ ዳኞችን ሹመት አጽድቋል፡፡ በተጨማሪም ምክር ቤቱ በሙስናና በብልሹ አሰራር እንዲሁም ከአቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ ክፍተት ያሳዩ ሰባት ዳኞችንም አሰናብቷል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት አፈ- ጉባዔ አቶ ላክደር ላክባክ ጉባዔው ሲጠናቀቅ እንደገለጹት የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ከመፍታት አኳያ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡ በተለይም የክልሉን ህዝብ የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የልማት ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ጥረት እንዲደረግ አስገንዝበዋል፡፡ በተለይም የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማጠናቀቅ ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡ ምክር ቤቱ ያጸደቀውን በጀትና የልማት እቅዶች በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆኑ ክትትልና ግምገማ ከማድረግ በተጨማሪ ከአስፈጻሚ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚያሻ አፈ ጉባዔው አስገንዝበዋል። አገራዊውን ለውጥ ተከትሎ የሴቶችንና የወጣቶችን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት መጠናከር ይገባዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም