ለጸጥታና ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሔ በጋራ ይሰራል…የደኢህዴን አመራሮች

71
ሐምሌ 20/2011 በሀገሪቱ ባለው የፀጥታና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ። በሃዋሳ እየተካሄደ ያለው የከፍተኛ አመራሮች የምክክር መድረክ የዛሬ ውሎው በቡድን ውይይት ትናንት በተነሱ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ድርጅቱ በበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የተገነባ እንደመሆኑ እስከ አሁን በተጓዘበት ሒደት ማንም ሊክደው የማይችል ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ድሎችን መጎናፀፍ ተችሏል። ሆኖም የድርጅቱ የቀድሞ ተራማጅነት ባህሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደከመ እንደመጣና የተፈጠረው የመስመርና የጎራ መደበላለቅ በተለይም በአመራሩ ዘንድ መታየቱን የቡድን ሪፖርቱ ላይ ተወስቷል። ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የእርስ በርስ መጠራጠርና ቀድሞ የነበረው የመደጋገፍ ልምድ መዳከም ኋላቀር ብሔርተኝነት በአመራሩ ጎልቶ መታየቱ ሰፊ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ለመገባቱ ምክንያት መሆኑም ተጠቁሟል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደኢህዴን ከስራ አስፈፃሚው ጀምሮ በሁሉም አመራሮች ዘንድ ተደጋጋሚ መርህ መጣስና በሁሉም ብሔረሰቦች የተመረጠ አመራር ለብሔሩ የሚወግንበት ሁኔታ መጉላቱም ተመልክቷል። አብዛኛው አመራር በየአካባቢው እመሰርተዋለሁ ባለው ክልል ውስጥ እራሱን መክተቱ ተገቢ አለመሆኑም በውይይቱ ተነስቷል። ደኢህዴንን እንደ ድርጅት ለማስቀጠል ሁሉም አመራር ከአሁን በኋላ ባሉት ጊዜያት ቁርጠኛ መሆን እንደሚገባ በጋራ ውይይቱ መስማማት ላይ ተደርሷል። ከፍተኛ አመራሩ ዛሬ ከሰአት በኋላ ጀምሮ ደኢህዴን ባስጠናው የክልል አደረጃጀት ጥናት ዙሪያ ውይይት ማድረግ ጀምሯል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም