የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የትምህርት ተቋማትና ኅብረተሰቡ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

77
ሐምሌ 20 /2011ዓ.ም  (ኢዜአ) የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ኀብረተሰቡ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የሳይንስና ከፍተኛ ተቋማት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ። ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ያስተማራቸውን 1 ሺህ 63 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል 206ቱ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው። በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እንዳሉት፤ በአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት የተደራሽነት፣ የጥራትና የፍትሃዊነት ችግሮች ይስተዋሉ ነበር። ባለፉት ዓመታት የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠንና ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ሲደረግ መቆየቱንና የከፍተኛ ትምህርት በፍጥነትና በከፍተኛ ደረጃ እንዲስፋፋ መደረጉን አስታውሰው፤ የሚሰጠውን ትምህርት ጥራት ለማሻሻል የሚረዱ መርሃግብሮች ተነድፈው ተግባራዊ መደረጋቸውን  ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ለትምህርት በሰጠችው የተለየ ትኩረትና ተደራሽነት በርካታ ወጣቶች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል። ''ከፍተኛ ትምህርትን ማስፋፋት፣ ጥራትና ፍትሃዊነትን በማረጋገጥ ሂደት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓይነተኛ ሚና ተጫውተዋል'' ያሉት ሚኒስትሯ በተለይ ተደራሽነታቸውን በማስፋት በኩል ለዜጎች የትምህርት ዕድልን እንደከፈቱ አብራርተዋል። በአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ከገቡት ተማሪዎች ውስጥ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑት በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ይህ ተሳትፎ ከሌሎች አገሮችጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ሂሩት፤ የግል የትምህርት ተቋማትን ተሳትፎ ለማሳደግ የፖሊሲ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ማደራጀት እንደሚገባ አመልክተዋል። በአገሪቱ ያሉ የተወሰኑ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በህግ አግባብና በኃላፊነት በመስራት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ቢሰሩም አብዛኛዎቹ ግን የጥራትና የህጋዊነት ችግር የሚስተዋልባቸው በመሆኑ የእርምት እርምጃ ሲወሰድ መቆየቱን አስረድተዋል። ጥራትን ለማሻሻል መንግስት ቀጣይነት ያለው ስራመስራት እንዳለበት የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ለዚህ ተግባር የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ኅብረተሰቡ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል። የግል ትምህርት ተቋማት ለአገር ዘላቂ ዕድገትና ልማት ኃላፊነት እንዳለባቸው የጠቆሙት ሚኒስትሯ  በመንግስት እምነት እንደተጣለባቸው በመገንዘብ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል። ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋፋት፣ጥራትን ለመጠበቅና ለማሻሻል እንዲሁም ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል። የወቅቱን የእድገትና የስራ ገበያ ፍላጎት የሚመጥን የማስተማርና የምርምር እንዲሁም የኅብረተሰብ አገልግሎት ላይ መስራት እንደሚጠበቅበት ፕሮፌሰር ሂሩት ተናግረዋል። የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አረጋ ይርዳው በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት ከተደራሽነት ባሻገር በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። ለመማር ማስተማር፣ ለጥናትና ምርምር የሚያግዙ ግብዓቶችን በየጊዜው እንዲሟሉ የሚያደርግ ስርዓተ ትምህርቱን የሚፈትሽ መሆኑንና ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በስምምነት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል። ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር ዘርፍ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ባካበቱት እውቀትና ክህሎት አገርን ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው የገለጹት ዶክተር አረጋ፤ ተመራቂዎች የጨለምተኝነት፣ የራስ ወዳድነትና የጠባቂነት መንፈስን ማስወገድ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው ያገኙትን እውቀት ለአገር ልማት ለማዋልና በእኩልነት መንፈስ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ለማገልገል እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን አሰልጥኖ ሲያስመርቅ የአሁኑ ለ36ኛ ጊዜ ሲሆን በቀጣይ በክልሎች በሚገኙ ካምፓሶቹ ያስተማራቸውን 505 ተማሪዎችን ያስመርቃል ተብሎ ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም