በትግራይ ዝናብ አጠር አካባቢዎች እርጥበትን ቋጥሮ ሰብል ለማልማት እየተሰራ ነው

48
መቀሌ ሐምሌ 20/2011የክረምት የዝናብ እጥረት በሚታይባቸው የትግራይ ክልል 17 ወረዳዎች አርሶ አደሮች እርጥበትን በመቋጠር ሰብል እንዲያለሙ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ። የሜትሮዎሎጂ አገልግሎት ማዕከል በበኩሉ፣አርሶ አደሮች አልፎ አልፎ የሚጥለው ዝናብ ተከትሎ የሚከሰተው ጎርፍ ለመያዝ የሚያስችሉ የውሃ ማቆሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ማሳ የማስገባት ስራ ማጠናከር አለባቸው ብሏል። በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የአዝርእት ልማትና የአፈር ለምነት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ለኢዜአ እንዳሉት በትግራይ በ17 ወረዳዎች በሚገኙ 136 ቀበሌዎች የዝናብ እጥረት እየታየ ነው። በበጋ ወቅት የተጀመረው እርጥበትን የማከማቸት ስራ አሁንም አርሶአደሮቹ በማሳቸው ላይ አጠናክረው እንዲያከናውኑ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በአካባቢዎች አልፎ አልፎ የሚጥለውን ዝናብ ከማሳ ውጭ እንዳይባክን በመንገድ ዳር የሚታየው ጎርፍ ወደ ማሳ የማስገባት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ ሰለሞን አስረድተዋል። በዚህም አርሶ አደሮች ማሳቸውን ፈጥነው በሚደርሱ ሰብሎች እንዲያለሙ ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ተብሏል። በደቡብ ምስራቅ ዞን እንደርታ ወረዳ የፈለገሰላም ቀበሌ አርሶአደር አሰፋ ግርማይ በሰጡት አስተያየት ፣በአካባቢያቸው እየተቆራረጠ ያለውን የክረምት ዝናብ ከማሳ እንዳይወጣ ከአካባቢያቸው አርሶአደሮች ጋር የእርከን ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በክልሉ ሜትሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ አቶ ዳርጌ ፍቃዱ እንዳስታወቁት እስካሁን ባለው የክረምቱ የዝናብ ሁኔታ ከክልሉ አጠቃላይ 35 በመቶ የሚሆነው ከመደበኛ በታች የዝናብ ስርጭት እየታየበት ነው። ባለፈው ወር በክልሉ 90 በመቶ የሚሆነው የኤልንኖ ክስተት ምልክቶች እንደነበረበት ያስታወሱት ኃላፊው፣ክስተቱ በአሁኑ ወቅት ወደ 57 በመቶ ቢወርድም ከዚህ ስጋት ነፃ አለመሆኑን ገልጸዋል። አልፎ አልፎ የሚጥለውን ዝናብ ወደ ማሳ የማስገባትና ከማሳ እንዳይወጣ ከመስራት በተጨማሪ እርጥበትን ለማከማቸት የሚያግዙና የውሃ ማቆር ስራዎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም