ኮሌጁ ከ3ሺህ 300 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ

78
አዳማ ኢዜአ ሃምሌ 20/2011 ሐራቤ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ3ሺህ 300 በላይ ተማሪዎች ዛሬ አሰመረቀ። በምርቃ ስነስርዓት ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ገላና ወልደሚካኤል እንደገለጹት ፈጣን ልማትን ለማሰቀጠል  ብቁ የሰው ኃይል ከሁሉም ጊዜ በላይ የሚያስፈልገን ወቅት ላይ እንገኛለን። ለዚህም የግሉ ሴክተር እያደረገ ያለው ተሳትፎ የላቀ መሆኑን ተናግረው ተመራቂዎች የራሳቸውን የስራ ድል በመፍጠር ሀገሪቱን ከድህነት ለማውጣት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል። “የህዝቦችን አንድነት በመጠበቅ በተቀናጀ መልኩ በልማቱ በመሳተፍ በሀገራቸውንና እራሳቸውን ለመለወጥ መሰራት ይኖርባቸዋል “ብለዋል። የክልሉ መንግስት ተመራቂዎች የስራ እድል ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፍ ገልጸዋል። “የአንጓዴ አሻራ ቀን በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ላይ በንቃት በመሳተፍ የጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ ፕሮግራም ማሳከት አለብን “ብለዋል። የሐራቤ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ባለቤት አቶ ፈይሳ አራርሳ በበኩላቸው ተመራቂዎች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ተግባር ላይ በማዋል እራሳቸውንና ሀገራቸውን ማገዝ እንደሚጠብቅባቸው ገልጸዋል። ኮሌጁ በተለያዩ የሙያ መስኮች አሰልጥኖ ዛሬ ያስመረቃቸው ተማሪዎች ለ16ኛ ጊዜ በዲፕሎማ፣ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ እንደሆነ አስረድተዋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ከግማሽ በላይ ሴቶች መሆናቸውን አመልክተዋል። ዳንኤል በቀለ ከተመራቂዎቹ መካከል አንዱ ሲሆን “ በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ አሰተማማኝ ሰላም ፣ ልማትና እድገት እንዲረጋገጥ ከመንግስት ጎን ሆነን እንሰራለን “ብሏል ። ወደ ምረቃው አዳራሽ ከመግባቱ በፊት በአዳማ በሚገኘው የኦሮሞ የባህልና የኮንፈረንስ ማዕከል ችግኝ መትከሉን የተናገረው ተመራቂ ዳንኤል የአረንጓዴ አሻራ ቀንም እንደሚሳተፍ ገልጿል። በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም