በትግራይ 20 ሚሊዮን ችግኞች ተተከሉ

106
መቀሌ ኢዜአ ሐምሌ 20/2011 የኢትዮጰያ የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም አካል በሆነው እንቅስቃሴ በትግራይ ክልል እስካሁን 20 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ገለጸ። የተተከለው በክልሉ ተዘጋጅቶ በክረምት ወቅት ለማከናወን ከታቀደው 80 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ ነው። ችግኞቹ የተተከሉት ከሐምሌ 3/2011 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን በ60ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መሆኑን በቢሮው የአከባቢ ጥበቃና የደን አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ሙኡዝ ኃይሉ ለኢዜአ ገልጸዋል። የችግኝ ተከላው 70 በመቶ በማይታረስ ተራራማ ስፍራ ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ በእርሻ መሬት ዳርና ዳር ነው። በክልሉ ባሉ 52 ወረዳዎችና ከተሞች አካባቢ በተካሄደው የችግኝ ተከላ ስራው ከ42 ሺህ የሚበልጥ ህዝብ መሳተፉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። የቀረው ችግኝ ደግሞ እስከ ሓምሌ 28/2011ዓ.ም ድረስ በተቀናጀ የህዝብ ርብርብ ተክለው ለማጠናቀቅ ታቅዷል። ዳይሬክተሩ በክልሉ ገጠርና ከተማ የሚገኝ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍልም የተዘጋጀውን ችግኝ በመትከልና እንዲፀድቅ በመንከባከብ አከባቢውን በአረንጓዴ ልማት ሊቀይር እንደሚገባ አሳስበዋል። የችግኝ ተከላና አያያዝ አስመልክተው አስተያየት የሰጡን የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የአከባቢና አየር ንብረት ተማራማሪ ዶክተር ግርማይ ገብረሳሚኤል ፣ችግኝ በመትከልና በመከባከብ የህብረተሰቡ ተሳትፎ በአርአያነት የሚጨጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል። “የተተከለውን ችግኝ እንዲፀድቅ ለመንከባከብ የሚደረገው ጥረት ግን አሁን እየተደረጋ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” ብለዋል ። ሐምሌ 22/2012 ዓ.ም በክልሉ አከባቢዎች እንደሚከናወንና ይህም ዘመቻው ‘’መለስ ለአረንጓዴ ልማት’’ በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አመልክቷል። ቢሮው እንዳለው በዕለቱም እስከ 12 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል። በትግራይ ክልል ባለፉት ዓመታት በተካሄደው የችግኝ ተከላ ከ92ሺህ በላይ ሄክታር በደን የተሸፈነ መሆኑ ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም