በቄለም ወለጋ ዞን የተከሰተውን የአሜሪካ መጤ ተምች ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው

1566

ጊምቢ ሰኔ 5/2010  በቄለም ወለጋ ዞን ስምንት ወረዳዎች የተከሰተውን የአሜሪካ መጤ ተምች ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ምንተስኖት አለሙ  እንደገለፁት ተምቹ በዞኑ በ150 ቀበሌዎች 12 ሺህ ሄክታር መሬት በተዘራ የበቆሎ ማሳ ላይ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ተከስቷል፡፡

ተምቹ  ወደ ሌላ አካባቢ  እንዳይዛመት ከግብርና ባለሙያዎችና ከአርሶ አደሮች የተውጣጣ ግብረ ሃይል በሁሉም ወረዳዎች ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ተምቹን በባህላዊ ዘዴ ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ ከ3 ሺህ  ሊትር በላይ ኬሚካል ለየወረዳዎች ተከፋፍሎ ርጭት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተምቹን በመከላከል ስራ እየተሳተፉ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል የጊዳሚ ወረዳ ባታ ቀበሌ ነዋሪ አቶ  ጅባ ዱጉማ  በሰጡት አስተያየት  ባለፈው አመት በበቆሎ አዝመራቸው ላይ የተከሰተውን ተምች ለመከላከል በልማት ቡድናቸው አማካኝነት ያከናወኑት ተግባር ውጤታማ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ካለፈው አመት ካገኙት ልምድ በመነሳት ዘንድሮም ተምቹ በምርታቸው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

አርሶ አደር መሀሪ ቀና በበኩላቸው ተምቹን በባህላዊ ዘዴ በመከላከል ምርታቸውን ለመታደግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ በ102 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከሚለማው የበቆሎ ሰብል  ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን  ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዞኑ ባለፈው አመት ተምች በ26 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ተከስቶ የነበረ ቢሆንም የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉ ታውቋል፡፡