በተስፋ የቀረው የተንዳሆ ስኳር…

128
አየለ ያረጋል (ኢዜአ) ….እንደ መንደርደሪያ… ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ምርት ካቆመ ስድስት ወራት ተቆጥሯል። ለግንባታው እስካሁን በርካታ ቢሊየን ብር ወጪ ሆኗል። ፋብሪካው ስራ ቢያቆምም ለሰራተኛ ደመወዝ ብቻ በስኳር ኮርፖሬሽን በኩል ከ35 ሚሊየን ብር በላይ በየወሩ ይከፍላል። ለምን? እንዴት? ተንዳሆተንዳሆ - በባለ ጊሌዎች መንደር፣ በድንቅነሽ ቅሪተ አጽም ባድማ፣ በታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ በአፋር ሃሩር የሚገኘው ‘ስመ ገናና’ ስፍራ ነው። ለአዲስ አበባ 670 ኪሎ ሜትር ይርቃል። ከዛ ይልቅ ከግማሽ በላይ ርቀቱ ቀንሶ ለጂቡቲ ወደብ 3 መቶ ኪሎ ሜትሮች ብቻ ይርቃል። በዘመነ ደርግ የተመሰረተ ሰፊ የጥጥ እርሻ የሚገኝበት፣ ከሩቅም ከቅርብም ወጣቶች ለጥጥ ለቀማ ወደስፍራ የሚተሙበት ነበር። ከ13 ዓመታት (በ1998 ዓ.ም) በፊት ነው። ከስድሳ ዓመታት በላይ እድሜ ያለውና በወንጂ ስኳር ፋብሪካ የጀመረው የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ በታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ላይ እጅግ ዘመናዊና ግዙፉን የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በመገንባት የኢንዱስትሪውን ታሪክ ደማቅ ለማድረግ ጥረት ተጀመረ። እናም ተንዳሆ ተበሰረ። ግዙፉ ተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክትን ዕውን ለማድረግ ወደስራ መግባቱን መንግስት ይፋ አደረገ። በተመሳሳይ በዱብቲ አካባቢ የሚገኘው ተንዳሆ እርሻ ልማት ወደ ስኳር አገዳ ልማት ሊዘዋወር መሆኑ ተረጋገጠ። ግዙፍ ተስፋ የተጣለበት ተንዳሆ ስኳር ተንዳሆ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ከተጀመረ 13 ዓመታት ነጎዱ። ፋብሪካው በአዋሽ ወንዝ ላይ በተገነባው (1 ነጥብ 8 ቢሊየን ኩብ ውሃ ይይዛል፤ 60 ሺህ ሄክታር መሬት ያለማል በተባለው) የተንዳሆ መስኖ ግድብ አማካኝነት እንዲለማ ታቀደ። ግድቡም በሚሌ፣ ዱብቲ፣ አሳኢታና አፋምቦ ወረዳዎችን በማካለል 50 ሺህ ሄክታር የስኳር አገዳ ልማት ለማልማት ታቀደ። በሁለት ምዕራፍ የሚገነባው ፋብሪካው በእያንዳንዳቸው በቀን 13 ሺህ ቶን በአጠቃላይ 26 ሺህ ቶን በቀን እንደሚያመርቱ፣ በሂደትም በዓመት እስከ ስድስት መቶ ሚሊዮን ኩንታል ስኳር እንደሚያመርቱ ተነገረ። ከስኳር ተረፈ ምርት 120 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ እንደሚያመርት፣ ከዚህም 76 ሜጋ ዋት የሚሆነው ከፋብሪካው ተርፎ ወደ ብሄራዊ ኤሌክትሪክ የኃይል ቋት ይገባል ተባለ። ሁለቱ ፋብሪካዎች (ቁጥር 1 እና 2) በድምሩ 63 ሚሊዮን ሊትር ኢታኖል ያምርታሉም ተብሏል። ፋብሪካው ወደ ሙሉ አቅሙ ሲገባ ለ50 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራልም ተብሏል። የግጦሽ መሬት የተወሰደባቸው አርብቶ አደሮች ካሳ እንደሚከፈላቸው፤ ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ የግጦሽ መሬት እንደሚለማላቸው፤ የስራ እድል እንደሚፈጠርላቸው ተነገራቸው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ የመንግስት ባለስልጣናት የአካባቢውን አርብቶ አደሮችን እየሰበሰቡ በተስፋ አጠገቧቸው። ከጅምሩ ዳፋ ያልተላቀቀው ፋብሪካ የተንዳሆ የቁልቁለት ጉዞ ከውጥኑ ነው። በጥናት ሳይሆን በሞራል/በወኔ ብቻ ወደስራ መግባቱን የመንግስት የስራ ኃላፊዎቹም ባለሙያዎቹም ያምናሉ። በችኮላ በመገባቱ ከፋብሪካ ቦታ መረጣ ጀምሮ ችግር እንዳለበት ይነገራል። በሞራል ወደ ስራ የተገባበት ተንዳሆ ግንባታው ከታቀደለት ጊዜ አራት ዓመት ዘግይቶ በ2001 ዓ.ም ተጀመረ። በሁለት ምዕራፍ ይከናወናል የተባለው ፋብሪካው ገና ከመጀመሪያው ዙር ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ አሸናፊዎች ቢለዩም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ለሌላ ሶስተኛ ድርጅት ተላልፎ መሰጠቱን የፋብሪካው ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከጨረታ ይልቅ በፖለቲካ ውሳኔ እድሉን ያገኘው ኦ.አይ.ኤ (Overseas Infrastructure Alliance) የተሰኘው የህንድ ኩባንያ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታውን ጀመረ። በ2001 ዓ.ም የጀመረው የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በ2007 ዓ.ም የሙከራ ምርት መጀመሩ ይፋ ሆነ። በወቅቱ የተነገረው የግንባታ ወጭም 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ነበር። ጥቅምት ወር ላይ 1 ሺህ 300 ኩንታል እንደሚያመርት ይፋ የሆነው ተንዳሆ ከአንድ ወር በኋላ (ህዳር 2007) ወደሙሉ የማምረት አቅሙ ይገባል ተብሎም ነበር። ሁለተኛው ምዕራፍም በሚያዚያ 2007 ዓ.ም ምርት እንደሚጀምር በወቅቱ ተዘግቦ ነበር። ዳሩ ግን ወቅቱ የምርጫ ወቅት ስለነበር ለህዝብ ስሜት መያዣ እንጂ ፋብሪካው እንዳልተጠናቀቀ የፋብሪካው የስራ ኃላፊዎች አረጋግጠዋል። የማምረቱ ብስራት የእፎይታ ጊዜ ሳይኖረው ለሁለት ወራት ብቻ አምርቶ ስራ ማቆሙ ተነገረ። (በ2 ወራት ውስጥ 118 ሺህ 123 ኩንታል እንደነበር በወቅቱ ኢዜአ ዘግቧል)። የሙከራ ምርቱም በቀን በተባለው የ13 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም አልነበረውም። ፋብሪካው ሳይጠናቀቅ እንዲጀምር መደረጉ፣ የታቀደለትን የምርት መጠን ማምረት አለመቻሉ ብቻ አይደለም ችግሩ። ሳይጠናቀቅ አምርት የተባለው ማሽን ተሰባብሮ ዕቃ መጥፋቱ ይነገራል። ጥገና እየተደረገለት ነው የቀጠለው። ፋብሪካው ተጠናቀቀ ተብሎ ከስራ ተቋራጩ ጋር ርክክብ አልተደረገም-እስካሁንም ድረስ። ፋብሪካው ተጠናቀቅ በተባለበት ሰዓት 13 ሺህ ቶን አገዳ መፍጨት እንደሚችል ተሞክሮና ዕቃ ከተበላሸም መለዋወጫ ለማቅረብ የውል ስምምነት ተደርጎ ማስረከብ ነበረበት።ይህ ባለመደረጉ ስራ ተቋራጩ ‘ከአራት ዓመታት በላይ ስትጠቀሙበት ከረማችሁ ወይም አስረጅታችሁ እንዴት አሁን አስረክባለሁ’ በሚል ርክክቡ ለማድረግ ስምምነት መጥፋቱን በስፈራው የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች አስረድተዋል። ለረጅም ዓመታት ስኬታማ የጥጥ አምራች የነበረውን ተንዳሆ እርሻ ልማት እንዲቆም ተደርጎ የተንዳሆ ስኳር አገዳ ልማት ተተካ። አገዳ ተከላ ተጀመረ። ፋብሪካው ሳይተከል መተከል የጀመረው አገዳ ለመታጨድ ደረሰ። ፋብሪካው የለምና ስድስት ሺህ ሄክታር የሚሆን አገዳም እንዲወገድ ተደረገ። ከአምስት ዓመታት በፊት 19 ሺህ ሄክታር መሬት በአገዳ ለምቶ እንደነበር መረጃዎች ይናገራሉ። ፋብሪካው ሲደርስ ደግሞ በተቃራኒው ሆነ። ዲዛይኑ 50 ሺህ ሄክታር አገዳ ለምቶ 26 ሺህ ቶን ስኳር በቀን ለማምረት ቢታቀድም አልተሳካም። ከ50 ሺህ 25 ሺህ ሄክታር ብቻ እንዲለማ ተወሰነ። 26 ሺህ ቶን የተባለው ዕለታዊ አገዳ የመፍጨት አቅሙ ወደ 13 ሺህ ዝቅ እንዲል ተደርጎ ተመሰረተ። ብድር የተወሰደው፣ ዕቃ የተገዛው፣ ቅድመ ዝግጅቱ የተደረገው ግን ለ26 ሺህ ቶን ዕለታዊ የስኳር ምርት ተብሎ ነበር። ከ50 ሺህ ሄክታር የአገዳ ማሳ ሌላ ለአካባቢው ነዋሪዎች 10 ሺህ ሄክታር የግጦሽ መሬት ይዘጋጃል ቢባልም እስካሁን አልተዘጋጀም። ለአገዳ ልማት በተወሰደው የአርብቶ አደሮች መሬት ምትክ ወይም ካሳ ይሰጣቸዋል ቢባልም አልተሰጠም። (የጎሳ መሪና የአካባቢው አመራር ለካሳ የተባለውን ገንዘብ ተጠቅመውበታል የሚሉም አሉ)። በ2010 ዓ.ም ዓ.ም ኢዜአ በሰራው ዘገባ በስፍራው በማህበር ተደራጅተው (ከ16 በላይ አገዳ አምራች አቅራቢ ማህበራት ተደራጅተው ነበር) አገዳ ለማብቀል ወደስራ የገቡ የአካባቢው ነዋሪዎች በውሃ እጥረት ምክንያት አገዳ ለማብቀል መቸገራችውን፣ በኋላም ፋብሪካው ለእነርሱ የገባላቸውን ቃል ለመክፈል ውል ማቋረጡን (መሬቱን በሌላ ሰብል ሸፍነው እንዲጠቀሙ አማራጭ መስጠቱን)፣ የተከሉት አገዳም በውሃ እጥረት መጥፋቱን፤ መሬቱም ስራ አቁሞ በመጤ አረም መወረሩን አረጋግጠው ነበር። ለክልልም ሆነ ለፋብሪካው ያቀረቡት ቅሬታም ውጤት ያለው ነገር አለማምጣቱም እንዲሁ። በርግጥ የህዝቡ ጥያቄ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ በየወቅቱ በስፈራው ለሚሄዱ የፌዴራል መንግስቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ቅሬታ ለማቅረባቸው በየጊዜው የተቀረጹ የስብሰባ ምስሎች ምስክር ናቸው። የፋብሪካው የስራ ኃላፊዎቹ እንደሚሉት ከቅርብም፤ ከሩቅም አርብቶ አደሮች ወደስኳር ማሳ እንስሳቶችን ያሰማራሉ። በዚህም አገዳ ማልማት ትልቅ ችግር ሆኗል። በ2008 ዓ.ም በነበረው የኤሊኖ ድርቅ አርብቶ አደሮች ለከብቶቻቸው ግጦሽነት ያገለገለው የተንዳሆ አገዳ ልማት እንደነበር ያስታውሳሉ። ዘንድሮም በተመሳሳይ የአገዳ ማሳው በአርብቶ አደሮች መጠቃቱን ይፋ አድርገዋል። ይህ ችግር የሚከሰተው ደግሞ ከጅምሩ ለግጦሽ የሚሆን የመኖ ማሳ አለመዘጋጀቱ እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የአፋር ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አሲያ ከማል ተንዳሆ ገና ከጅምሩ ሲመሰረት የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ አለማድረጉንና ማህበረሰቡ የባለቤትነት ስሜት ማጣቱን ገልጸዋል። ዛሬም ያልተፈቱ ከስራ እድል ፈጠራ፣ ከአካባቢው እንስሳት ጤና እክልና ተጠቃሚነት ላይ ማህበረሰቡ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉትና የክልሉ መንግስትም ጥያቄውን እንደሚጋራው አረጋግጠዋል። ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ኩብ ውሃ መጠን የያዘ፣ 60 ሺህ ሄክታር አገዳ የሚያለማ ግድብ ቢገደብለትም የአገዳ እጥረት ችግር ግን ፋብሪካውን ጦም አሳድሮታል። ፋብሪካው የሚገኝበት (አሳይታ) ስፍራና የስኳር አገዳው ተጭኖ የሚመጣበት ስፍራ ከ11 እስከ 70 ኪሎ ሜትር ይርቃል። (ቅርብ ይገኛል የተባለው 11 ኪሎ ሜትር እንደሚርቅ ይጠበቃል-አንዳንዶች ለዚህ ጸሃፊ የነገሩት ቅርብ ቦታ የተባለው 20 ኪሎ ሜትር ይርቃል)። በነገራችን ላይ ሌሎች የኢትዮጵያ ስኳር ፋብሪካዎች (እነ መተሃራ) ሩቅ የሚባለው የአገዳ ማሳ 10 ኪሎ ሜትር አይበልጥም። እናም የአገዳ አቅርቦት ችግር ትልቁ ፈተና ሆናል። ለዚህም ቢበዛ በቀን ከ4 ሺህ 300 ቶን በላይ ስኳር ማምረት አይችልም ይላሉ። ፋብሪካው ከዓመት ዓመት የማምረት አቅሙ ተሻሽሏል (ከዓመት ዓመት ችግሩን እየፈታን ነው ይላሉ የስራ ኅላፊዎቹ)። በ2011 ዓ.ም 4 ሺህ 300 ቶን አገዳ በቀን መፍጨቱ ተገልጿል። ፋብሪካው የአገዳ አቅርቦቱ ቢሻሻል እስከ 8 ሺህ ቶን ስኳር የማምረት አቅም እንዳለው ይገልጻሉ። ወደፊት ችግሮች እየተፈቱ ከሄዱ ደግሞ እስከ 10 ሺህ ቶን ሊደረስ እንደሚችል ይናገራሉ። እስካሁን ግን ለአራትና አምስት ቀናት በትራክተር አገዳ ተጓጉዞ ነው በቀን 4 ሺህ 300 ቶን አገዳ የሚፈጨው። ''በቀን ግን ማጓጓዝ የሚቻለው ከ2 ሺህ 500 ቶን አገዳ አይበልጥም ይላሉ'' ሰራተኞቹ። ሌላው ችግር የ’ባጋስ’ አቅርቦት ችግር ነው። ፋብሪካው አገዳ ለመፍጨት የሚጠቀመው ኃይል በራሱ ባጋስ (ከሸንኮራ አገዳ ገለባ የሚመነጭ ሃይል) ነው። 24 ሰዓት ለመፍጨት ኃይል ለማመንጨት የሚውል በቂ ‘ባጋስ’ አልቀረበለትም። ባጋስ የሚቀርብለት ለ16 ሰዓት ሲሆን ቀሪውን ስድስት ሰዓት ደግሞ በ’ፈርነስ ኦይል’ ነው የሚጠቀመው። ይህ አዋጭ አልሆነም። እናም ፈርነስ እያቃጠለ ለመጠቀም ደግሞ አዋጭ አይደልም በሚል ፋብሪካው ስራ አቁሟል። ምክንያቱ ደግሞ ‘አንድ ፈርነስ ኦይል (የማቅለጫ ዘይት) በ16 ወይም 17 ብር እንገዛለን። በቀን ከ600 እስከ 700 ሺህ ብር ለፈርነስ ኦይል እንጠቀማለን። የምናመርተው ትርፍ ግን ከ500 ሺህ ብር አይበልጥም” ይላሉ አንድ የስራ ኃላፊ። ዘመናዊ ፋብሪካዎች በተጓዳኝ ሃይል አምርተው ለራሳቸውም ተጠቅመው ለሌላም አካል በመሸጥ ገቢ ማግኘት የነበረባቸው ሲሆን እስካሁን ግን የትኛውም ዘመናዊ የስኳር ፋብሪካ ኤሌክትሪክ ሃይል ሽጦ ገንዘብ አላገኘም” ሲሉ ያክላሉ። ተንዳሆ በበቂ ሁኔታ ባጋስ ካገኘ ለአሳይታ፣ ሰመራ የሚበቃ ኤሌክይሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም አለው። ፋብሪካው ከሶስት ቦይለሮች አንዱን ነው እስካሁን የሚጠቀመው። ኢ-ቫጋስ ከተጠቀመበት እስከ 20 ሜጋ ዋት ማመንጨት እንደሚቻል ነው ባለሙያዎች የሚገልጹት። ፋብሪካው አሁን ላይ ብራውን (ቡናማ) ስኳር ነው የሚያመርተው። ምርቱም ለአገር ውስጥ ገበያ ይውላል እንጂ ኤክስፖርት አይሆንም። ምርቱ ሰልፈር ስለሌለው (በኖራ ነው የሚመረተው) ለጤና ተስማሚ እንደሆነ ባለሙያዎች አረጋግጠዋል። ፋብሪካው የማጣሪያ ማሽን (ሪፋይነሪ ፓርት) ቢኖረውም እስካሁን ስራ አልጀመረም። ተንዳሆ ከአገር ውስጥ የተትረፈረፈ ምርት አቅርቦት ባሻገር ለውጭ ገበያ ለማቅረብና የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የመሆን ዓላማ ነበረው። ‘ጽድቁ ቀርቶ በቅውጡ በኮነነኝ’ እንዲሉ ተንዳሆ ግን ወደ ውጭ ቀርቶ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚሆን ስኳር ምርት ናፍቆታል። ባለፈው ዓመት 80 ሺህ፣ ዘንድሮ ደግሞ 47 ሺህ ቶን ስኳር ማምረቱን የፋብሪካው የስራ ኃላፊዎች ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል ከስኳር ፋብሪካው ጎን ለጎን ለሰራተኞች መኖሪያ የሚሆን ቤቶች ለመገንባት የነበረው የተንዳሆ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ነበር። 12 የመኖሪያ መንደር ተገንብቷል። ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት 3 ሺህ የመኖሪያ ቤቶች በዱብቲ ብቻ መገንባታቸውን ተገልጾ ነበር። የስኳር ኮርፖሬሽን መረጃዎች ደግሞ በአጠቃላይ 8 ሺህ 997 የመኖሪያ ቤቶችና 146 የአገልግሎት መስጫ ብሎኮች መገንባታቸውን ይጠቁማል። ዛሬ ላይ በ12 መንደሮች ተገንብተው የነበሩ የመኖሪያ ቤቶች እየፈራረሱ መሆኑን የስራ ኃላፊዎቹ አረጋግጠውልኛል። ቤቶቹ በየቦታው ተገንብተው ያለአግባብ የህዝብ ሀብት መባከኑ ብቻ ሳይሆን የተሰሩበት ቦታና የፋብሪካው ቅርበት ጉዳይ ሌላው ፈተና ነው። ሰራተኛ ወደ ፋብሪካ ሲገባ (ከኃላፊ በስተቀር) በእግር መጓጓዝ እንዳለበት በፋብሪካ አሰራር ደንብ ይመከራል። የተንዳሆ ፋብሪካ የሰራተኛ መኖሪያ ቤቶች የተገነቡበት ስፍራ ግን ቅርብ የተባለው 7 ኪሎ ሜትር ነው። የትም አገር የሌለ አሰራር እንደሆነ የሚገልጹት የፋብሪካው የስራ ኃላፊዎች፤ ሰራተኞች በጊዜ ወደስራ እንዳይገቡ፣ ፋብሪካውን ለማክሰር ታስቦ የተሰራ ይመስላል ባይ ናቸው። እናም አንድ ሰራተኛ ወደኋላ ቢቀር መኪና ተልኮ መምጣት ግድ ይላል - ካልሆነ ስራው አይሰራም። በሌላ በኩል ደግሞ ፋብሪካው የተሰራበት ቦታም ለጎርፍ ተጋላጭ ነው። አሁንም የጎርፍ መከላከያ ስራ (ዳይክ) ተሰርቶለት ነው ወደስራ የገባው። ሌላው የመለዋወጫ አቅርቦት ችግር ነው። ይህ ችግር በርግጥ የተንዳሆ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ስኳር ፋብሪካዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠመ ያለ ችግር መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። በፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ለብዙ ዓመታት መስራታቸውን የገለጹት አንድ የስራ ሃላፊ፤ በዓመት 40 ሚሊየን ብር ለመለዋወጫ ብቻ ይመድብ እንደነበር ይገልጻሉ። አሁን ላይ ለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በዓመት የሚመደበው የመለዋወጫ በጀት ግን 8 ሚሊየን ብር ብቻ እንደሆነ ያብራራሉ። በስኳር ልማት በርካታ ፕሮጀክቶችን እየገነባች ያለችው ኢትዮጵያ የመለዋወጫ አምራች ፋብሪካ መገንባት ዘላቂ መፍትሔ እንደሆነ ባለሙያዎች ይመክራሉ። በአጠቃላይ የተንዳሆ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ግድቡንም፣ የቤት ፕሮጀክቶችን፣ እርሻ ልማቱን ጨምሮ እስካሁን ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበታል። በየወሩ ለሰራተኛ ደመወዝ የሚከፈለው 35 ሚሊዮን ብር በግማሽ ዓመት ብቻ 210 ሚሊዮን ብር ባክኗል ማለት ነው። በዚህ ከቀጠለ በዓመት ከ420 ሚሊዮን ብር ይባክናል እንደማለት ነው። በቢሊዮን የውጭ እዳ ያለበት ፋብሪካ (የፋብሪካው አንድ የስራ ሃላፊ መረጃ መሰረት 232 ሚሊዮን ዶላር የውጭ እዳ አለበት) ካለስራ በየወሩ በአስርት ሚሊዮኖች መክፈሉ አገራዊ ኪሳራ እንደሆነ ምስክር አያስፈልግም። የቀጣይ እጣ ፈንታውስ? ፋብሪካው ስራ ካቆመ ግማሽ አመት አልፎታል። ፋብሪካው ፖለቲካዊ ውሳኔ እንጂ የቴክኒክ ችግር እንደሌለው የስራ ኃላፊዎቹ ያብራራሉ። ትልቅ ፋብሪካ ነው። ፋብሪካው ሲቋቋም የዕቃ ጥራት ችግር እንደሌለበት የስራ ኃላፊዎቹ ያብራራሉ። የተሰራበት ዕቃው (ማቴሪያል) ቻይና ሰራሽ ከሆኑ ሌሎች ስኳር ፋብሪካዎች በተሻለ ተመራጭ መሆኑን ገልጸዋል። (የመንግስት የልማት ደርጅቶችን ወደግል ለማዞር ባለው አገራዊ እንቅስቃሴ ስኳር ፋብሪካዎች የመጀመሪያ ዙር ወደግል የሚዛወሩ እንደሆበነ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ተንዳሆም በውጭ አገሮች የሚገኙ ኩባንያዎችን ትኩረት መሳቡ ተነግሯል) ለአካባቢው አርብቶ አደሮች የግጦሽ መሬትና መኖ ማሳ ካልተዘጋጀ በፋብሪካው የሚለማው አገዳ ቢተከልም ለመታጨድ ዋስትና የለውም። ከወልድያ ጀምሮ በሁሉም ከቅጣጫ አርብቶ አደሮች በተለይ የድርቅ ጊዜ እንስሳትን በአገዳው ልማት ላይ ያሰማራሉ። ይህ ችግር የሚቀረፈው ለአካበቢው የግጦሽ መኖ ጉዳይ እልባት ሲያገኝ ብቻ እንደሆነ እሙን ነው። የመኖና ግጦሽ መሬት በተጓዳኝ ካልተሰራ በእንስሳት የመወረር ችግሩን ማስወገድ አዳጋች ነው። በመሆኑም በተገባው ቃል መሰረት ለእንስሳቱ መኖ የግጦሽ መሬት ማዘጋጀትና ማልማት ቁልፍ ጉዳይ ነው። የአገዳ አቅርቦቱና ፋብሪካው አይጣጣሙም። ፋብሪካው አሁን ባለው የሰው ሃይል፣ መንገድ፣ 13 ሺህ ቶን አገዳ መፍጨት አይቻልም። ስለዚህም ሜካናይዝድ ወይም ዘመናዊ ሰፋፊ እርሻ ስርዓትን መፍጠር እንደሚገባ ኃላፊዎቹ ይናገራሉ። ለፈጣን ትራንስፖርት የመንገድ መሰረተ ልማት ማስተካከል ያስፈልጋል። ምክንያቱም እስከ 70 ኪሎ ሜትር በትራክተር (በኪሎ ሜትር 1 ሊትር የሚፈጁ ተሽከርካሪዎች) ለማጓጓዝና ፋብሪካ ለመመገብ ለነዳጅ የሚወጣው ወጭ ግዝፈት ብቻ ሳይሆን ስፍራው ከፍተኛ ሙቀት ያለበት በመሆኑ የማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ሙቀቱ እስከ 47 ድግሪ ሴንቲግሬድ ሲደርስ በቀላሉ ጎማቸው እየተቃጠለ ተጨማሪ ወጪ እየጠየቁ መሆኑ ተገልጿል። በሌላ በኩል የአካባቢው ማህበረሰብ የሚያለማቸውን እርሻዎች ወደ አገዳ ምርት እንዲለወጡ ማድረግ (outgrowing) አንዱ መፍትሔ መሆኑም ይነሳል። ''ከሁሉም በላይ ዘለቂ መፍትሔ የሚሆነው በክልልና ፌዴራል መንግስት (ስኳር ኮረፖሬሽን) መግባባት ሲኖር ነው'' ይላሉ። ስኳር ኮርፖሬሽን የአርብቶ አደሮች ከብት ጥቃት ጉዳይ ከአቅሙ በላይ መሆኑን ሲገልጽ ይሰማል። ከላይ ስማቸውን የጠቀስኳቸው የክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ደግሞ በፋብሪካው ሳቢያ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ጉዳይ ምላሽ እንዲያገኝ ይፈልጋሉ። አሁንም ፋብሪካው ስራ የሚቀጥል ከሆነ በህብረተሰቡ ይሁንታ መመስረት፣ ጥያቄዎች መመለስ እንዳለባቸው ኃላፊዋ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም