የተቀዛቀዘውን የማዕድን ዘርፍ ለማበረታታት የተቋቋመው አገራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ስራ ጀመረ

51
አዲስ  አበባ  ሀምሌ 19/2011 ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የመጣውን የማዕድን ዘርፍ እንደገና ለማሻሻል የተቋቋመው የባለድርሻ አካላት የቅንጅት አሰራር አስተባባሪ ኮሚቴ ስራ ጀመረ። ኮሚቴው ከኢትዮጵያ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይና ከኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን የተዋቀረ ሲሆን ዋና አላማው ባለ ድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሰርተው የዘርፉን አገራዊ አስተዋጽኦ ማሳደግ ነው። የማዕድን ዘርፍ የባለ ድርሻ አካላት የቅንጅት አሰራር አስተባባሪ ኮሚቴ ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በውጭ ምንዛሬ ማዳንና የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ዘርፉ የነበረው አገራዊ ኢኮኖሚ ጉልህ ነበር። ለአብነትም በ2004 ዓ.ም ዘርፉ 654 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት ከቡና ቀጥሎ የተመዘገበ ሲሆን በ2011 ዓ.ም ግን ከዘርፉ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ 44 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብቻ ነው። ለዚህም በዋናነት ዘርፉ የሚመራበት የህግ ማዕቀፎችና መመሪያዎች ግልፅና አምራቹን የሚያበረታቱ አለመሆናቸው እንደ አንድ ምክንያት ቀርቧል። ከዚህ በተጨማሪም በባለ ድርሻ አካላት መካከል ቅንጅት አለመኖር፣ የማዕድን ሃብትን የመለየትና የማሳወቅ ችግር፣ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት የግብአትና የክህሎት ድጋፍ አለማድረግ ዋና ምክንያት እንደሆኑ ኮሚቴው አመልክቷል። እነዚህን የተለዩ ክፍተቶች ለመሙላት በአሁኑ ወቅት ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲ እንዲኖረውና የህግ ክፍተቶቹ እንዲሻሻሉ የማድረግ ስራው እያለቀ መሆኑንና በዚህ በጀት አመት ስራ ላይ እንደሚውል ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪም አስተባባሪ ኮሚቴው ከጉምሩክ፣ ከፀጥታ አካላትና ከሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር እንዲኖር በማድረግ ለአምራቹ፣ አቅራቢውና ላኪው የቴክኖሎጂ፣ የክህሎት እንዲሁም የአቅርቦት ድጋፍ በማድረግ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቀነስ ስራ መጀመሩን ጠቁሟል። የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው ተሰራ እንዳሉት፤ ኮሚተው እነዚህን ስራዎች በመስራት በ2011 በጀት አመት 44 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የነበረውን የዘርፉን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በተያዘው በጀት አመት ወደ 265 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ነው። ''የማዕድነ አምራቾች ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር በመፍጠርም 200 ሺህ የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ ይዘናል'' ሲሉም ሰብሳቢው ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም