በ"ሳሎን" ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ ከስጋት ነፃ አድርጎናል - ነዋሪዎች

80
አምቦ ሰኔ 5/2010 በሳሎን ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ ከስጋት ነፃ እንዳደረጋቸው በምዕራብ ሸዋ ዞን የኤጄሬ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የቀበሌው አስተዳደር በበኩሉ የድልድዩ መገንባት የአካባቢውን ነዋሪዎች የረዥም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ደበላ ጨመዳ በሰጡት አስተያየት የሳሎን ወንዝ በክረምት ወቅት ከአቅም በላይ ስለሚሞላ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ተጽእኖ ሲያሣድር መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በወንዙ ላይ የተገነባው ድልድይ ክረምት ሲመጣ ወንዝ ለመሻገር ያለባቸው ስጋት መቀረፉን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደር ጃረሶ ሚደግሳ በበኩላቸው ቀደም ሲል በክረምት ወቅት  በሚፈጠር የወንዝ ሙላት ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችን ለማከናወን ሲቸገሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ " ከቤታችን ወጥተን ራቅ ያለ ቦታ ስንሄድ ወንዝ ሞልቶ ይጠብቀናል የሚል ስጋት አሁን የለብንም " ያሉት አስተያየት ሰጪው ድልድዩን የገነባላቸውን አካል አመስግነዋል ። ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አጸደ ሰንበታ በበኩላቸው  የድልድዩ መገንባት በፈለጉት ሰዓት ያለስጋት ወደ ገበያም ሆነ ዘመድ ጥየቃ  ለመንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡ በወረዳው የባሶ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ጋዲሣ ደበሌ እንዳሉት የድልድዩ መገንባት የአካባቢውን ነዋሪዎች የረዥም ጊዜ ጥያቄ የመለሰ ነው ብለዋል፡፡ ድልድዩን በ350 ሺህ ብር ወጪ አስገንብታ  ለወረዳው ያስረከበችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ሌሎች የልማት ድርጅቶችም ይህን አርአያ በመከተል ከመንግስት ጎን በመቆም ልማት ባልደረሰባቸው ቦታዎች ላይ ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል ፡፡ የወረዳው ቤተ ክህነት ኃላፊ መልዐከ ህይወት አባ ወልደ ሰንበት ደበሌ በበኩላቸው ቤተ ክርስቲያንዋ ከዚህ ቀደምም በተለያዩ የልማት ስራዎች በመሳተፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጓን ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም በተለያዩ  የልማት ስራዎች ላይ ተሳትፎዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም