ደኢህዴን ለኢኮኖሚ ማነቃቂያ ፕሮግራም ተግባራዊነት እንደሚሰራ ገለጸ

49
አዲስ አበባ ሰኔ 4/2010 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ያሳለፋቸው የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ፕሮግራም ውሳኔዎች ትክክልና አስፈላጊ በመሆናቸው ለተግባራዊነቱ እንደሚሰራ ደኢህዴን አስታወቀ። የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ሊቀመንበር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ዛሬ ለ5 ቀናት የተካሄደው የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ኮንፈረንስ አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግጫ  ኢህአዴግ ለኤርትራ ያቀረበው የሰላም ጥሪ ወቅታዊና ተገቢ ነው። የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ኢህአዴግ እያደረገ ያለውን ለውጥ በመገምገም ከመግባባት ላይ ደርሰዋል። በቅርቡ የኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባስቀመጠው የሰላም ጥሪና የኢኮሚ ማነቃቃት አቅጣጫዎች ይዘትና ጠቀሜታ ላይ ደኢህዴን ከከፍኛ አመራሩ ጋር መክሮ ተግባብቶባቸዋል። የኢኮኖሚ ማሻሻያው አገሪቱ “አሁን ባለችበት የለውጥ እንቅስቃሴ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ የዕድገታችን ማነቆዎች እንዲፈቱ ምርታማነት እንዲጨምርና የውጭ ምንዛሬ ግኝት ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል'' ብለዋል። ይሄንን ፋይዳ በመገንዘብ ደኢህዴን ለተግባራዊነቱ እንደሚሰራ በኮንፈረንሱ ማረጋገጡን ጠቅሰዋል። ኢህአዴግ የአልጀርስ ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ የአገሪቱ ጥቅም በሚያስከብር መልኩ ለመፈፀም በመወሰኑ ደኢህዴን ድጋፉን እንደሚሰጥና ለተግባራዊነቱ እንደሚታገል አረጋግጠዋል። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010  ባካሄደው ጉባዔ እንዳለው  በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉ በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴል እና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ የሚተላለፉ ናቸው፡፡ የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክሲዮን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም