ምሰራቅ ጎጃም ውስጥ በ51 ሄክታር ኩታገጠም ማሳ ላይ የቡና ችግኝ ተተከለ

110

ደብረ ማርቆስ ኢዜአ ሐምሌ 17 ቀን 2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን እየጣለ ያለውን የክረምት ዝናብ በመጠቀም 133 ሺህ የቡና ችግኞች መተከላቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
ችግኞቹ የተተከሉት በ51 ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳ ላይ ነው።

በመምሪያው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ ተሾመ ይመር ለኢዜአ እንደገለፁት በክረምቱ ወቅት በ290 ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳ ላይ 725 ሺህ የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ።

የአየር ንብረታቸው ለልማቱ ተስማሚ በሆኑ ሶስት ወረዳዎች ላይ ተከላው እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

“እየተተከሉ ያሉት የቡና ችግኞች በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የመስጠት ባህሪ ያላቸው ናቸው” ብለዋል”

በልማቱ ከ2 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ነው።

እንደ ባለሙያው ገለጻ ባለፈው ዓመት በ60 ሄክታር ኩታገጠም ማሳ ላይ የተተከሉ 200 ሺህ የቡና ችግኞች እድገታቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

በማቻከል ወረዳ የየውላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደሳለሽ መኩሪያው ኩታገጠም በሆነ አንድ ሄክታር ከሩብ ማሳቸው ላይ የቡና ልማት እያካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

“ከዚህ በፊት በሩብ ሄክታር ማሳ ላይ ከተከልኩት የቡና ችግኝ ጥሩ ምርት በማግኘቴ ልማቱን በኩታ ገጠም ማሳ ማስፋፋት ጀምርያለሁ” ብለዋል ።

ከሰብል ጎን ለጎን በጀመርኩት የቡና ልማት ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸው የገለጹት ደግሞ በጎዛምን ወረዳ የለቅለቂታ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ይርዳው ወርቁ ናቸው።

አርሶ አደሩ እንዳሉት ዘንድሮም ኩታገጠም በሆነ አንድ ሄክታር ማሳ ላይ ችግኝ እየተከሉ ናቸው።

በምስራቅ ጎጃም ዞን  ካለፉት ስድስት ዓመታት ጀምሮ  2ሺህ 40 ሄክታር በቡና ልማት መሸፈኑ ታውቋል።