የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በመጪው ዓርብ ይጀመራል

69
የጋምቤላ ኢዜአ -ሐምሌ 17 ቀን 2011 የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አራተኛ የስራ ዘመን ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ በመጪው ዓርብ እንደሚጀመር የምክር ቤቱ አፈ- ጉባኤ አስታወቁ ። አፈ- ጉባኤው አቶ ላክደር ላክባክ ለኢዜአ እንደገለጹት የምክር ቤቱ ጉባኤውን ከሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በጋምቤላ ከተማ ይካሄዳል። ጉባኤው የክልሉን የ2011 በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር፣ የኦዲት ቢሮና የጠቅላይ ፍርድ ቤት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት አዳመጦ እንደሚያጸድቅ አመላክተዋል። በክልሉ ለ2012 የበጀት አመት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድና የማስፈፀሚያ በጀት ላይ ውይይት በማደረግ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል። የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችንና ሹመቶችን መርምሮ እንደሚጸደቅም ገልጸዋል። “በጉባኤው ማጠናቀቂያ የአረንጓዴ ልማት አሻራን በማስመልከት የችግኝ ተከላ ይካሄዳል” ብለዋል። በጉባኤው የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ከ300 በላይ የክልል፣የዞንና የወረዳ አመራር አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣የኃይማኖት አባቶች፣ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉ አፈ-ጉባኤው አስታውቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም