የአርብቶ አደር የከፊል አርብቶ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የሚተገርብበት ስትራቴጂ ተዘጋጀ

86
ጅግጅጋ ሐምሌ 16 / 2011የአርብቶ አደር የከፊል አርብቶ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በተሟላ መልኩ የሚተገርብበት ስትራቴጂ መከለሱን የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ገለጸ። ሚኒስቴሩ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመተባበር የከለሰውን ስትራቴጂ በጅግጅጋ ይፋ ተደርጓል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሐርላ አብዱላሂ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ስትራቴጂው የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ አኗኗር ባገናዘበ መልኩ የተቀረጸ ነው። ስትራቴጂውን በአዲስ መልክ የተከለሰው ላለፉት 12 ዓመታት ትግበራው ውጤታማ  ባለመሆኑ ነው ብለዋል። ስትራቴጂው የአርብቶ አደር ማህበረሰብን መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለማዳረስ ብሎም ለማጠናከር እንደሚያግዝ ሚኒስትር ዴኤታዋ አስረድተዋል። በተለይ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የእናቶችና የህፃናት ጤና ሽፋን፣ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እንዲሁም የጤና ተቋማት አገልግሎትን ለማዘመን ትኩረት መስጠቱን አስታውቀዋል። የሴቶች የልማት ቡድን በመጠቀምና ሴት የአርብቶ አደር ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በማሰማራት ስትራቴጂው እንደሚተገበርም ወይዘሮ ሰሐርላ አስታውቀዋል። የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዩሱፍ መሐመድ የስትራቴጂው መሠረታዊ ዓላማ የጤና አገልግሎት በሁሉም አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ነዋሪዎች ማድረስ መሆኑን ገልጸው፣በተሟላ መልኩ እንዲተገበር የሚመለከታቸው አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በክልሉ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ከተተገበረ ወዲህ በ16 ፓኬጆች ከ216 ሺህ በላይ ሞዴል ቤተሰቦች ተጠቃሚ መሆናቸውንም አመልክተዋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የ93 ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና አግባብ ያላቸው አካላት ተሳትፈዋል። ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በመከላከል ላይ ያተኮረውን የጤና ፖሊሲ ለመተግበር እንዳስቻላት ይታወቃል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም