በክላስተር በመደራጀት በመስራታችን ምርትና ገበያ በማግኘት ተጠቃሚ ሆነናል-አርሶ አደሮች

139

ሐምሌ 16 / 2011 (ኢዜአ) በክላስተር በመደራጀት በመስራታቸው የሚያመርቱትን ምርት እንዳሳደገላቸው በምስራቅ ሸዋ ዞን የሊበን ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሑሴን በምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ወረዳ በክላስተር ተደራጅተው ጤፍ በማምረት የተሰማሩ አርሶ አደሮች እንቅስቃሴን የጎበኙ ሲሆን መንግስት የሚያደርግላቸውን ድጋፍ እንዲቀጥልላቸው አርሶ አደሮቹ ጠይቀዋል።

ከአሁን ቀደም በአንድ አካባቢ ባልተደራጀ ሁኔታ የተለያዩ ሰብሎችን ይዘሩ እንደነበርና በዚህም ውጤታማ እንዳልነበሩ የተናገሩት አርሶ አደሮቹ በአሁኑ ወቅት በአንድ አካባቢ ጤፍን ለማምረት በጋራ በመደራጀታቸው እርስ በርስ ለመማማር እንደረዳቸው ተናግረዋል።

መንግስት የሙያ፣ የማዳበሪያ፣የአረም ማጥፊያና ሌሎች ለግብርና የሚያገለግሉ ድጋፎችን እንደሚያደርግላቸውና በዚህም ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

ቀደም ብሎ በሄክታር ከ8 እስከ 10 ኩንታል ይገኝ እንደነበርና አሁን ግን ከ25 እስከ 30 እያገኙ መሆኑንም እንዲሁ።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም እርሻቸው ማደራጀት ሁሉም እኩል እንዲሰሩ፣እንዲተባበሩና ተጠቃሚነታቸውም የተቀራረበ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ለአርሶ አደሩ ከስልጠና ጀምሮ እስከ ምርት ማምረት ከዚያም የገበያ ትስስር እስከ መፍጠር ድረስ ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

በቀጣይ የዚህ አይነት የዘመናዊ ግብርና እንቅስቃሴን በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም እንሰሳት እርባታ ላይ ለማምጣትም ስራ ተጀምሯል ብለዋል።

በሃገሪቷ ምርትን ለማሳደግ በሚደረገው በክላስተር የማደራጀት ወይም ሌሎች በግብርናው ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴወችን በየቦታው ያሉ የዘርፉ ባለሙያዎችና ሁሉም ዜጋ ከአርሶ አደሩ ጋር በመሆን በእውቀቱና በጉልበቱ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል ሚኒስትሩ።