የከተሞችን ገጽታ በሚቀይርና በረሃማነትን በሚከላከል ስራ ለመሳተፍ በመቻላችን ልዩ ስሜት አድሮብናል- የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሰራተኞች

76
ሀምሌ 16/2011 (ኢዜአ)የከተሞችን ገጽታ የሚቀይሩና በረሃማነትን ለመከላከል የሚያስችሉ ችግኞችን ለመትከልና ለመንከባከብ ዝግጁ መሆናቸውን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሰራተኞች ገለጹ። በመጪው ሀምሌ 22 በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የ“አረንጓዴ አሻራ ቀን” በአንድ ጀምበር  200 ሚዮዬን ችግኝ ለመትከል መታቀዱ የሚታወቅ ነው። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሰራተኞች እንደተናገሩት የስራ መስካቸው ከተሞችን ማስዋብና መቀየር በመሆኑም ጭምር በችግኝ ተከላ ስራው የራሳቸውን አሻራ ለማኖር በመቻላቸው ደስተኛ ሆነዋል። ወጣት ታዬ ሰለሞን  በአረንጓዴ አሻራ ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ ታሪክ የሚጽፍበት አጋጣሚ በመሆኑ ያሳደረበትን መነሳሳትና ዝግጁነት ይናገራል። በሚኒስቴሩ ስር በተቋቋመው የወጣቶች ህብረትም የተተከሉ ችግኞችን በየወሩ በመሄድ አመቱን ሙሉ ለመንከባከብ ዕቅድ ይዘናል ሲልም ተናግሯል። በአገር አቀፍ ደረጃ ሌሎች ወጣቶችን የማነሳሳትና የማበረታታት ስራዎች እንደሚሰሩም ገልጿል። በዕለቱ በሚካሄደው የችግኝ ተከላና በቀጣይነት ለሚደረገው የእንክብካቤ ስራዎች ያላትን ፈቃደኝነትና ዝግጁነት የገለጸችው ደግሞ ወይዘሪት ዝናሽ መኮንን ናት። አቶ ጀማል ኑረዲን በበኩላቸው በመርሃ ግብሩ መሳተፋቸው አገርን የማገልገልና በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የእራሳቸውን ሚና የማበርከት ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ  የተለየ ስሜት አሳድሮብኛል ብለዋል። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ላቀው አበጀ በበኩላቸው በዕለቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚገኙ 2 ሺህ 56 ከተሞች ውስጥ  38 ሚሊዮን ችግኞች እንዲተከሉ እየተሰራ ነው ብለዋል። በመጪው ሰኞ ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት በጋራ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ቢልቢሎ በሚባል አካባቢ ከ10 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። አቶ ላቀው እንደገለጹት ለችግኝ ተከላ ስራው አስፈላጊ የሆኑ የትራንስፖርትና ሌሎች ግብዓቶችን የማሟላትና የግብርናና የጤና ባለሙያዎችን ዝግጁ የማድረግ ስራዎች እየተሰራ ነው። እንደ አቶ ላቀው ገለጻ የሚኒስቴሩ ግብ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ለሚፈለገው ግብ ማድረስ ነው ። በዚሁ መሰረት በተተከሉ ችግኞች ላይ ለ3 ዓመታት ክትትል እንደሚደረግና ያልጸደቁ ችግቾችን የመተካት እቅድ መያዙንም ተናግረዋል። በዘላቂነትም ችግኞችን የመንከባከብ ስራውን በባለቤትነት የሚያከናውን በሚኒስቴሩ ስር የሚገኝ ተቋም መኖሩንም ጠቁመዋል። በአጠቃላይ በክረምቱ የችግኝ ተከላ ስራ በከተሞች ብቻ 760 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል እቅድ መኖሩንም አክለዋል። ሚኒስቴሩ ከተሞችን ጽዱ፣ ውብና አረንጓዴ ለማድረግ ከሚያከናውናቸው ስራዎች መካከልም በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ከተሞች በከተማ ግብርና ፣ በተቋማትና በግለሰቦች ግቢና አካባቢ፣ የማህበራትና የጋራ መኖሪያ ቤቶችና ሌሎች ስፍራዎች ላይ  ችግኞች እንደሚተከሉም ጠቁመዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም