ኢትዮ-ቴሌኮም ከ 9 ቢሊዮን ብር በላይ የተከማቸ ብድር መክፈሉን አስታወቀ

84
አዲስ አበባ ኢዜአ ሐምሌ 16/2011 ኢትዮ-ቴሌኮም ባለፉት ሶስት ዓመት ሳይከፍል የቆየውን ውዝፍ የ9 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር እዳ መክፈሉን አስታውቀ። ኢትዮ ቴሌኮም የ2011 በጀት  ዓመት የስራ አፈጻጸሙን በተመለከተ ዛሬ ለጋዜጠኞ  መግለጫ ሰጥቷል። በበጀት ዓመቱ ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ያስታወቀው ኢትዮ-ቴሌኮም ይህም ከታቀደው አንፃር 79 በመቶ አፈጻጸም ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት እንፃር ሲሰላ የ5 ነጥብ 6 በመቶ እድገት  ማሳየቱን ነው የተገለፀው። የኢትዮ - ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሂወት ታምሩ  በመግለጫቸው እንዳስታወቁት፤ ከበጀት ዓመቱ አንዱ እንደ ተቋም ስኬት የሚቆጠረው ሳይከፈል የቆየ ውዝፍ እዳ መከፈሉ ነው ብለዋል። በዚህም ባለፉት 3 ዓመታት ሳይከፈል የቆየ 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር መክፈሉን  አስታውቀዋል። የብድር ከፈላው መፈፀሙ ኢትዮ ቴሊኮም ከተለያዩ አለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋራ ለሚያደርገው የጋራ ተጠቃሚነትን ላማከለ ግንኙነት አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። ተቋሙ በቀጣይነትም ከተለያዩ አለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋራ ለሚያደርገው ግንኙነት በጋራ ለመስራት  የሚያስችሉ አሰራሮችን በመተግበር ላይ መሆኑን ወይዘሪት ፍሬህይወት ተናግረዋል። ለአብነትም በቻይና ከሚገኙ የፋይናስ ተቋምትጋር ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ላይ መደረሱን ገልፀው ተቋማቱ በቀጣይ ከኢትዮ ቴሎኮም ጋር በብድር ጉዳዮች ላይ ለመደራደር ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል። ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ 16 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ግብር መክፈሉን ተናግረው ከዚህ ውስጥ  4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የሚሆነው ለዓመታት ያልተከፈለ  ውዝፍ የግብር ክፍያ መሆኑንም አስረድተዋል። ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ላይ ከ43 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ላይ መድረሱን  የተናገሩት ወይዘሪት ፍሬህይወት ይህም ከእቅዱ አንጻር ሲሳላ  95 በመቶ አፈፃጸም አሳይቷል ብለዋል። ይህም አጠቃላይ የቴሌኮም ስርጸት በመጠኑ 44 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን እና  ከዚህ ውስጥ ሞባይል ድምጽ 41 ነጥብ 92 ሚሊዮን መሆኑንም ተናግረዋል። የዳታ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚ ደግሞ 22 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሲደርስ መደበኛ  ስልክ ደግሞ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደንበኞች መሆናቸው ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም