የችግኝ ተከላ ዘመቻ የግብርና ክፍለ-ኢኮኖሚውንና የኢኮኖሚ ሽግግሩን እንዲያግዝ መሰራት አለበት ተባለ

61
ሀምሌ 14/2011 (ኢዜአ) በአገሪቱ እየተከናወነ ያለው የችግኝ ተከላ ዘመቻ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውንና የኢንዱስትሪ ሽግግሩን እንዲያግዝ መሰራት አለበት አሉ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ተማሪዎች። የአካዳሚው ሠራተኞችና 110 የአካዳሚው የአንደኛ ዓመት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ዛሬ በሱሉልታ ከ1 ሺህ 500 በላይ ችግኞችን ተክለዋል። ተማሪዎቹ በአሁኑ ወቅት በዘመቻ እየተተከለ ያለው ችግኝ የግብርና ክፍለ-ኢኮኖሚውንና አገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ የምታደርገውን ሽግግር እንዲያግዝ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል። ከ80 ከመቶ በላይ የማህበረሰቡ መተዳደሪያና ክፍለ-ኢኮኖሚ መሠረቱ ግብርና  መሆንና የሚመረተውም ወቅት ተጠብቆ በሚገኝ ዝናብ ስለሆነ ቀጣይነት ላለው እድገትና ስኬታማ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን ደኖች ጥበቃ እንዲደረግባቸው አሳስበዋል። በአካዳሚው የፐብሊክ ፖሊሲ ተማሪ ዛኪር አብደላ እንደሚለው "የኢኮኖሚ መሠረታችን አብዛኛው ዝናብ ተጠብቆ ስለሚከወን ችግኝ መትከል ለክፍለ-ኢኮኖሚው   ዋስትና ስለሚሆን በእንክብካቤ መያዝ አለበት"። ይህም አገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ክፍለ-ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር መሳካት መልካም አጋጣሚ ስለሚፈጥርላት ሁሉም ለችግኝ ተከላና ደኖችን በብዛት ለያዙ ፓርኮች ትኩረት እንዲሰጥ ተማሪ ዛኪር ጠይቋል። ሌላው የፐብሊክ ፖሊሲ ተማሪ መስፍን ሞጋ ደግሞ ችግኝ መትከል የሚመከር ቢሆንም ከአካባቢው ስነ ምህዳር ጋር ተጣጥሞ መተከል እንዳለበትና የኢኮኖሚ መሠረት ግብርናና ምርታማነቱን እንዲጨምር በጥናት ቢሆን ይላል። እንደተማሪ መስፍን፤ ችግኞች በአካባቢው የአየር ሁኔታ፣ የአፈሩን ለምነት ለመጨምር እንዲሁም የውሃ መጠን ታሳቢ ተደርጎ እንዲተከልና ለተከላ ከመዘጋጀታቸው በፊትም በደንና አካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ሙያዊ እገዛ እንዲከናወን ነው የጠየቁት። በተማሪዎች በቀረበው የችግኝ ተከላ ጥያቄ መሠረት ለተከላው ግቢያችንን መርጠናል ያሉት በአካዳሚው የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ አቶ ወንድዬ ለገሰ ይህም የአካዳሚው ተማሪዎችና ሠራተኞች ለመንከባከብና የመማር ማስተማሪያ አካባቢን ውበት እንደሚያላብስ አስታውቀዋል። በዚህም ግቢው የተሻለ ሳቢነት እንዲኖረው ባህር ዛፍን እየቆረጡ ለአካባቢው ስነ-ምህዳር በሚስማሙ የችግኝ ዝርያዎች እየተኩ መሆናቸውን አቶ ወንድዬ የተናገሩት። እንዲሁም አካዳሚው በአረንጓዴ አሻራ ቀንም ተጨማሪ ችግኞችን በመትከል ለክብረ ወሰኑ እውን መሆን አስተዋጽኦ ለማድረግ መዘጋጀቱን አቶ ወንድዬ ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም