በአቶ አማረ አምሳሉ የክስ መዝገብ በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች የክስ መቃወሚያቸውን አቀረቡ

72
ሀምሌ 16/2011 (ኢዜአ) በአቶ አማረ አምሳሉ የክስ መዝገብ በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች የክስ መቃወሚያቸውን ዛሬ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ የወንጀል ችሎት አቅርበዋል። የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በእነ አቶ አማረ አምሳሉ የክስ መዝገብ በ10 የቀድሞ የኢትዮ-ቴሌኮም የስራ ሃላፊዎች ሰራተኞች ላይ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል። ክሱ 1ኛ ተከሳሽ አቶ አማረ አምሳሉ(በሌሉበት)፣ 2ኛ ተከሳሽ አቶ ወልደጊዮርጊስ ወልዱ (በሌሉበት)፣ 3ኛ ተከሳሽ አቶ ኢሳያስ ዳኘው፣ 4ኛ ተከሳሽ አቶ አብዱልሀፊዝ አህመድ፣ 5ኛ ተከሳሽ አቶ ማስረሻ ጥላሁን፣ 6ኛ ተከሳሽ አቶ ሰይፈ ኃይለስላሴ(በሌሉበት)፣ 7ኛ ተከሳሽ አቶ ጸጋዬ መኮንን(በሌሉበት)፣ 8ኛ ተከሳሽ አቶ አይተንፍሱ ወርቁ፣ 9ኛ ተከሳሽ አቶ ጌታሁን ያሲን (በሌሉበት) እንዲሁም 10ኛ ተከሳሽ አቶ ሳሙኤል ፈጠነ(በሌሉበት) ስልጣንን ያላግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል የተመሰረተ ነው። ከ259 ሚሊዮን ብር በላይ በኢትዮ-ቴሌኮም፣ በህዝብና በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የሚልም ተካቷል። ዐቃቤ ሕግ በክሱ እንዳመለከተው ተከሳሾች በሶማሌ ክልል የሞባይል ማስፋፊያ ግንባታ የአገልግሎት ግዥ ውል በሚከናወንበት ወቅት ለራሳቸው ብሎም ለብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ የኢትዮ-ቴሌኮምን የግዥ መመሪያ ወደ ጎን በመተው  ያለ ውድድር  221 ሚሊዮን 804 ሺህ 693 ብር ላይ ጉዳት በማድረስ እንዲሁም በኢትዮ-ቴሌኮም የግንባታ ርክክብ ዝርዝር ስፔስፊኬሽንን መሰረት ሳያደርግ 51 ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ ርክክብ በመደረጉ በዚህም ከ69 ሚሊዮን ብር በላይ ከደንብና መመሪያ ውጭ እንዲከፈል በማድረግ የተፈጸመ ወንጀል ነው። በተጨማሪም 161 የመፀዳጃ ቤቶችና 161 የጥበቃ ቤቶች የግንባታ ሂደታቸው ሳይጠናቀቅ እንደተጠናቀቁ በማስመስል ርክክብ በማድረግ በአጠቃላይ 295 ሚሊዮን 586 ሺህ 120 ብር በላይ ጉዳት በማድረስ በከባድ የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውንም የቀረበባቸው ክስ ያሳያል። ከዚህ በፊት በነበረው ችሎት 3ኛ ተከሳሽ አቶ ኢሳያስ ዳኘው 4ኛ ተከሳሽ አቶ አብዱልሀፊዝ አህመድ 5ኛ ተከሳሽ አቶ ማስረሻ ጥላሁን እና 8ኛ ተከሳሽ አቶ አይተንፍሱ ወርቁ ችሎት ቀርበው የቀረበባቸው ክስ መነበቡ የሚታወስ ነው። ተከሳሾች የተነበበልንን የክስ ፍሬ ነገር ተገንዝበናል በክሱ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ማቅረብ እንድንችል ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን ባሉት መሰረት ችሎቱ ለዛሬ የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። በዚሁ መሰረት 3ኛ ተከሳሽ አቶ ኢሳያስ ዳኘው 4ኛ ተከሳሽ አቶ አብዱልሀፊዝ አህመድ 5ኛ ተከሳሽ አቶ ማስረሻ ጥላሁን እና 8ኛ ተከሳሽ አቶ አይተንፍሱ ወርቁ በዛሬው የችሎት ውሎ በቀረበባቸው ክስ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በጠበቆቻቸው በኩል አቅርበዋል። በቀረቡት ክሶች ላይ እያንዳንዱ ተካሳሽ ያደረሱት ጉዳት በግልጽ አልተቀመጠም፣ በክሱ ላይ የቀረቡ የግዢ እና ሌሎች አዋጆች እና የኢትዮ ቴሌኮም የግዢና ፖሊሲ መመሪያ ከተያዘው ጉዳይ ጋር አግባብነት የለውም፣ በእያንዳንዱ ተካሳሾች ላይ የቀረበው ክስ በዝርዝርና ግልጽ በሆነ መልኩ መቀመጥና በማስረጃ መደገፍ አለበትና የክስ አቀራረቡ የስልጣን ደረጃና ሃላፊነት ጋር በተያያዘና በክሱ ላይ የተጠቀሱ ጊዜያት በግልጽ መቀመጥ አለባቸው የሚሉ ሀሳቦች በክስ መቃወሚያዎቹ ቀርበዋል። በክሶቹ ላይ እርስ በእርስ የሚጣረሱ ጉዳዮች በመኖራቸው ተካሳሾች የቀረበባቻውን ክስ በግልጽ ተረድተው ለመከላከል አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸውም ተከሳሾቹ ገልጸዋል። በክሱ ላይ እ.አ.አ የተቀመጡ ጊዜያቶች በኢትዮጵያውን አቆጣጠር ተተርጉመው እንዲቀመጡም ያመለከቱ ሲሆን 8ኛ ተከሳሽ አቶ አይተንፍሱ ወርቁ በክሱ ላይ የተከሰስኩበት ወንጀል ከአንድ እስከ ሰባት ዓመት የሚያስቀጣ በመሆኑ ከህግ አንጻር የዋስትና መብት የማያስከለክል በመሆኑ የዋስትና መብቴ ይከበርልኝ ብለዋል ። በአጠቃላይ ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ዐቃቤ ህግ የክስ ማሻሻያ እንዲያደርግ ተካሳሾች ጠይቀዋል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ የወንጀል ችሎት በበኩሉ  የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያና በክስ መቃወሚያው ላይ የዐቃቤ ህግ ምላሽን ተመልክቶ ብይን ለመስጠት ለነሐሴ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም