ታሪካዊቷ ችግኝ

128
ምናሴ ያደሳ( ኢዜአ) ሀምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከመቱ ከተማ ተነስቼ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ከተጓዝኩ በኋላ አጋሮ ከተማ ደረስኩ ። በዚህ ዕለት በከተማው በሚካሄደው አንድ ለየት ያለ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ላይ ተገኝቻለሁ ። በዕለቱ የነበረው የችግኝ ተከላ መርሀግብር የተካሄደው የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የአጋሮ ከተማ አስተዳደር በጋራ ባዘጋጁት የሰላምና የልማት ኮንፍራንስ ማጠናቀቂያ ላይ ነው። የኮንፍራንሱ ተሳታፊዎች ፣ የአጋሮ ከተማና አካባቢዋ የሀይማኖት አባቶች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከ10 ሺህ በላይ ችግኞችን ተክለዋል። በዕለቱ ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ አንዷ ችግኝ ከሁሉም የበለጠ ትኩረቴን ሳበችው ። ሁሉም ሰው የየራሱ ችግኞችን እየተከለ ቢሆንም እኔን ጨምሮ አብዛኛውን ሰው ግን በአግራሞት የሚመለከታት ያቺው አንዷን ችግኝ ነው ። አዎን ! ችግኟ እውነትም የብዙሃኑ ትኩረት የመሳብ አቅም ነበራት ።ከፈላችበት ላስቲክ ተፈልቅቃ ቋሚ ቦታዋ ወደ ሆነው ጉድጓድ ያመራችው በሶስት የሃይማኖት አባቶች መዳፍ ተደግፋ ነበር ። በመልካም ሁኔታ እንድትፀድቅም እየመረቁ ከእርጥቡ ለም  አፈር ጋር እንድትዋሃድ አድርገዋታል ። ችግኟን በጋራ የተከሉት የኦርቶዶክስ ህይማኖት አባት ቄስ መላዕከ ገነት ካሴ፣ የጅማ ዞን ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ጸሀፊ ፓስተር ሰለሞን በልሁና የአጋሮ  ከተማ የእስልምና ሀይማኖት አባት ሀጂ ራያ አደም ናቸው። የሀይማኖት አባቶቹ ችግኟን በጋራ መትከላቸው በደንብ ከተገነዘብን በርካታ መልዕክቶች አለው። በተባረኩ ሶስት የጋራ እጆች  የተተከለችው ችግኝ በጊዜ ሒደት ወደ ትልቅ ዛፍነት ስትቀየር የአብሮነት፣የፍቅር የመቻቻልና የአንድነት ምልክት ተደርጋ የብዙዎች መሰባሰቢያ ትሆናለች የሚል ተስፋ አሳድራለች ። የሰላም፣የመቻቻልና የአብሮነት ተምሳሌት ተብላ በሰላምና የልማት ኮንፍራንሱ ላይ በሀይማኖት አባቶች በተመሰገነችው አጋሮ ከተማ ላይ የአብሮነትና የአንድነት ቅርስ የሆነችው ችግኝ በጋራ መዳፎች እንድትቆም ተደርጓል ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጎማ ወረዳና አጋሮ ከተማ ቤተክህነት ሀላፊ ቄስ መላዕከገነት ካሴ ችግኟን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል። ”ይህቺ በጋራ የተከልናት ችግኝ ትጸድቃለች ፣ምልክትም ትሆናለች ።” እሳቸው እንዳሉት በጋራ የተከሉት ችግኝ ኢትዮጵያውያን  በቋንቋ፣በሀይማኖትና በማንነት ሳይለያዩ ለሀገራቸው ሰላምና ልማት በጋራ እንዲቆሙ የሚያስተምር ነው። ”ይህቺን ችግኝ ተክዬ ወዲያውኑ ልርቃት አይደለም ከአፈር ያኖርኳት”ያሉት ቄስ መላዕከ ገነት በየጊዜው ተመላለሰው በመንከባከብ አርአያነት ያለው ተግባር ለማከናወን ዝግጁ ናቸው ። ችግኝ መትከል የአንድ ወቅት ስራ ብቻ ሳይሆን ከሀይወታችን ጋር ቀጥታ ግንኝነት  ያለው በመሆኑ እንደ ባህል ልናዳብረው ይገባል የሚል መልእክት አስተላልፈዋል ። በተለይ ወጣቶች ከተለያዩ አልባሌ ሱሶች ተላቅቀው ችግኞችን ተክለው ቢንከባከቡና ሀገሪቱ ከንትርክና ከጭቅጭቅ የፀዳች የፍቅር ፣ የመረዳዳት እና የመቻቻል ሀገር ለመገንባት ቢሰሩ ዋጋው በሰማይም ሆነ በምድር ከፍ ያለ እንደሆነ ነበር ያስገነዘቡት ። ይህቺ በሶስቱ የህይማኖት አባቶች በጋራ የተተከለችው ችግኝ ለአጋሮ ከተማ የተበረከተች ውድ ስጦታ ናት ተብላለች ። ቄስ መላአከ ገነት እንዳሉት ”ችግኝ መትከል ልጅ ወልዶ እንደማሳደግ ነው።  ችግኝ ተክሎ ሳይንከባከቡ መቅረት ደግሞ ልጅ ወልዶ እንደመጣል ነው።” ህብረተሰቡ ይሄንን  በሚገባ ተገንዝቦ የተከላቸውን ችግኞች ተከታትሎ በእንክብካቤ የማሳደግ ሃላፊነት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል ። ሌላኛው የሀይማኖት አባት ፓስተር ሰለሞን በልሁም በችግኝዋ ዙሪያ የሚከተለውን ሀሳብ ሰጥተዋል ። ዜጎች ያለ ምንም ልዩነት በሀገራቸው ሰላምና ልማት እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲሰሩ የተለያዩ የሀይማኖት አባቶች አርአያነታቸውን አሳይተዋል ።  ህብረተሰቡም ይህንኑ በመከተል የቆየ እሴታችን መጠበቅ አለበት ባይ ናቸው ። ” ዛሬ በጋራ የተከልናት ችግኝ ቋሚ ትምህርት ቤት ሆና እንድታገለግል እንፈልጋለን” ሲሉም አክለዋል ። የችግኝ ተከላ ስራን ጨምሮ መልካም እሴቶች እንዳይረሱ እንደ ባህል የዘወትር ተግባር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን መክረዋል ። የአጋሮ ከተማ የሀይማኖት አባት ሀጂ ራያ አደም በበኩላቸው ለህብረተሰቡ በተለይም ለወጣቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።ችግኝ መትከል የአየር ንብረት መዛባትን ከመከላከል ባለፈ ለሁሉም የልማት ስራዎች መሰረት በመሆኑ ህብረተሰቡ በንቃት ሊሳተፍ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት። ”ሀገር ሰላም ከሆነች፣ የተራቆቱ አካባቢዎች በደን ከተሸፈኑ፣ በህብረተሰቡ መካከል ፍቅር፣አንድነትና መቻቻል ከጎለበተ ሀገር ያድጋል የህብረተሰቡ ኑሮም ይሻሻላል” ነው  ያሉት። በሀገራችን በስፋት እየተከናወነ ያለው የችግኝ ተከላ ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ የመጣውን የደን ሽፋን ወደ ነበረበት አንደሚመልሰው አያጠያይቅም ።ይህ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጡን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ፋይዳው የጎላ ነው ። በተለይ ከአለማችን በህዝብ ብዛት ከፍተኛን ቁጥር የያዙት ቻይና እና ህንድ ያላቸውን የሰው ሀብት በመጠቀም በሁሉም የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን መሸፈናቸው በአሁኑ ወቅት ለደረሱበት የእድገት ደረጃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ይነገራል። ቻይና ከ 50 አመታት በፊት የደን ሽፋኗ ከአጠቃላይ ስፋቷ 8.6% ብቻ የነበረ ሲሆን በዚህም ልማቷን ለማሳደግ ትልቅ ተግዳሮት ተፈጥሮባት ነበር ።ይህንን በመገንዘብ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎቿ በየአመቱ ችግኝ እንዲተክሉ በማድረግ በአሁኑ ወቅት ሽፋኑን ከ 22 ከመቶ በላይ ማድረስ ችላለች ቻይና ከ20 ዓመታት በፊት በየአመቱ ከ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለው እንጨትና የእንጨት ውጤቶችን ከውጪ ታስገባ የነበረ ሲሆን የደን ሽፋኗ በመጨመሩ ምክንያት የውጪ ምንዛሪ ወጪዋን በማስቀረት የሀገር ውስጥ ደን መጠቀም ጀምራለች። በችግኝ ተከላ ዘመቻው የተራቆተ የነበረውን የቻይና ታላቁ ግምብ አካባቢ በተለያዩ የዛፍ አይነቶች በማስዋብ ከአለም ትልቁ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ተችሏል ። በሀገራችንም የደን ችግኝ ተከላው በብዙ መስኮች የነበረውን ችግር እንደሚቀርፍ ተስፋ ተጥሎበታል። በተለይ ሀገሪቱ ያላትን የውሀ ሀብቶች ከደለል ነጻ በማድረግ እየተከናወኑ ላሉት የኤሌትሪክ ማመንጫ ግድቦች ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። የአየር ንብረት መዛባትን በመከላከል በቂ የዝናብ ስርጭት እንዲኖር የደን መስፋፋት ፋይዳው የላቀ ነው ። በተለይ በቡናና በተለያዩ የቅመማ ቅመም ምርቶች በሚታወቁ አካባቢዎች ላይ ጥራት ያለው ምርት ለማምረት ደን ወሳኝነት አለው። በመሆኑም የጀመርነውን የደን ልማትና የችግኝ ተከላ ተግባር ሀገራችንን በብዙ እርምጃዎች ወደፊት የሚያራምዳት ነውና አጠናክረን እንቀጥልበት መልእክታችን ነው ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም