የፓርቲዎች ውህደት ለምርጫ ቦርድ ስራ እንደሚያቀል ተገለጸ

60
ሀምሌ 16/2011 (ኢዜአ) ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ውህደት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሰራር ላይ ያለውን ጫና የሚቀንስ መሆኑን ቦርዱ አስታወቀ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራር በቅንጅትና በግንባር መፍጠር ዙሪያ ያዘጋጀውን ስልጠና ዛሬ ሰጥቷል። የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ውህደት ወይም የሚፈጥሩት ግንባር የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሰራር ላይ ያለውን ጫና  ይቀንሳል። ''በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተናጠል ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር ከመስራት ይልቅ ወደ በውህደትና ግንባር ከመጡ ፓርቲዎች ጋር መስራት ይቀላል'' ብለዋል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት ወይም ግንባር እንዲፈጥሩ የሚያደርጉ ህጎችና ደንቦችን  እያወጣ መሆኑን የገለጹት አቶ ውብሸት ወደፊት ተግባራዊ የሚደረጉ ህግና ደንቦችም አሉ ብለዋል። እንደ አቶ ውብሸት ገለጻ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ የሰፋ ነው ማለት በፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት ሳይሆን  ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ዓላማና ፕሮግራም ያላቸው ፓርቲዎች ውህደት ወይም ግንባር ፈጥረው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው። በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ 107 የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መግባቢያ የሆነውን የቃልኪዳን ሰነድ ፈርመዋል። በአነቃቂ ንግግራቸው የሚታወቁት የስነ አእምሮ ህክምና ባለሙያው ዶክተር ምህረት ደበበ በፓርቲዎች ውህደትና ግንባር መፍጠር ዙሪያ የመነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል። ፓርቲዎች ውህደት ወይም ግንባር በሚፈጥሩበት ወቅት ሊከተሏቸው ስለሚገባቸው የውህደት ምሶሶዎች፣ ህጎችና ውስንነቶች ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም