ቤተክርስቲያኗ የሃይማኖት ተቋማት የኅብረትና የፍቅር ትምህርት እንዲሰጡ ጠየቀች

69
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 16/2011 በኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ ሠላም እንዲሰፍን የሃይማኖት ተቋማት የኅብረትና የፍቅር ትምህርት እንዲሰጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አሳሰበች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው የእርክበ ካህናት ጉባዔ በሠላም ጉዳይ አተኩሮ ለመስራት ውሳኔ ኣሳልፎ ነበር። በወቅቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናትና ምዕመናን ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም አገር አቀፍ የሠላምና አንድነት ኮሚቴም ተቋቁሟል። በኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድ ሠላምና ትብብር እንዲፈጠር የተቋቋመው ኮሚቴ የ52ቱ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንተ ቤተ-ክርስቲያን በተገኙበት የመጀመሪያ ጉባዔውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሰጡት ቡራኬ "የሃይማኖት ተቋማት የሠላም ምንጮች ናቸው" ብለዋል። በህዝቦች ዘንድ ሠላም እንዲሰፍን፤ ፍቅር፣ አንድነትና ትብብር እንዲጎለብት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት እንዲሰብኩም ጠይቀዋል። ሠላምን ማስፈን የሁሉም ምዕመን ድርሻ ቢሆንም የቤተክርስቲያን አባቶችና መምህራን ቅድሚያ መስራት "ይጠበቅብናል" ነው ያሉት። "ፀሎታችን ብዙ ነው፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ አልደረሰም ወይስ ምን ሆነ ዛሬም ችግር ውስጥ የሆንነው?" ያሉት ፓትሪያርኩ "አሁንም ህሊናችንን ሰብሰብ አድርገን ወደራሳችን መመለስ ይገባናል" ብለዋል። የሃይማኖት ተቋማት አባቶችም በተሰማሩባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ምዕመናንን ማህበራዊና መንፈሳዊ እሴት ማጎልበት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። አቡነ ማትያስ "ስለ ሠላም እየተሰበከ ሠላም የጠፋው ከመልካም የህሊና ዳኝነት ይልቅ መጥፎውን በመከተላችን የመጣ ነው" ብለዋል። በኢትዮጵያ ሠላም፣ ልማት፣ ዕድገትና ትብብር እንዲጎለብት ሁሉም በፀሎትና በትጋት ለሠላም ዘብ እንዲቆምም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም